በሞሮኮ የመሬት መንቀጥቀጥ በአንድ ከፍል ይማሩ የነበሩ ተማሪዎቹ በሙሉ ሞተዋል ተባለ
አስተማሪያቸው “ወደ መንደራቸው ሄጄ እያዳንዱን በስም እየጠራሁ ስጠይቅ ሁሉም ሞተዋል ተባልኩ” ብላለች
በሞሮኮ ባሳለፍነው ሳምንት በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ 3 ሺህ ገደማ ሰዎች ሞተዋል
በሳለፍነው ሳምንት በሞሮኮ ያጋጠመውን ከባድ ርእደ መሬት ተከትሎ 3 ሺህ ገደማ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
በርዕደ መሬት አደጋው ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ ህጻናት የሚገኙነት ሲሆን፤ በአንድ ከፍል ይማሩ የነበሩ 32 ተማሪዎቹ በሙሉ መሞታቸውን መምህርታቸው ለቢቢሲ ተናግራለች።
መምህርት ነስረን አቡኤልፈዴል ነዋሪነቷ ማራካሽ ሲሆን፤ ተራራማዋ አዳሴል ግን የምታስተምርበት ትምህርት ቤት መገኛ ነች።
የአረባኛ እና ፈረሳይኛ አስተማሪ የሆነችው መምህርት ነስረን አቡኤልፈዴል ተማሪዎቿን ለመፈለግ ወደ ተራራማዋ አዳሴል ባቀናችበት ወቅት የሰማችውን አስደንጋች ዜና ማመን ከባድ ሆኖባታል።
መምህርቷ በአንድ ክፍል ውስጥ ይማሩ የነበሩ እድሜያቸው ከ6 እስከ 12 የሆኑ 32 ተማሪዎች ሁሉም መሞታቸውንም ሰምታለች።
የቋንቋ መምህርቷ ነስረን አቡኤልፈዴል ተማሪዎቿን “ልክ እንደ መላእክት ናቸው” በማለት የምትገልጽ ሲሆን፤ ከድህንት ጋር እየታሉ የሚማሩ ቢሆንም ለሰው ክብር ያላቸው እና አዲስ ነገር ለመማር ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነበር ብላለች።
ከተማሪዎቿ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ከፍል ውስጥ የነበረቸው አርብ ምሽት ርእደ መሬቱ ከመከሰቱ ከ5 ሰዓታት በፊት እንደነበረም መምህርት ነስረን አቡኤልፈዴል ታስታውሳለች።
“ከተማሪዎቼ ጋር በነበረን የመጨረሻ ከፍል የሞሮኮ ብሄራዊ መዝሙርን ስንማማር እና ስንለማመድ ነበር፤ ሰኞ ጠዋት በሁሉም ተማሪዎች ፊት ብሄራዊ መዝሙሩን ለማቅረብ እቅድ ነበረን” ብላለች መምህርቷ።
መምህርት ነስረን አቡኤልፈዴል ምንም እንኳን የተረጋጋ ድምጽ ቢኖራትም፣ ከፍተኛ ሲቃ ውስጥ እንደሆነች ያስታውቋል። “እንቅልፍ አልተኛም፤ አሁንም ድንጋጤ ውስጥ ነኝ” ብላለች።
“ሰዎች እኔን እድለኛ እንደሆንኩ እድርገው ይቆጥራሉ፤ እኔ ግን ከዚህ በኋላ ኑሮዬን እንዴት መቀጠል እንዳለብኝ እንኳ አላውቅም ስትልም ተናግራለች።
የአስተማሪነት ስራዋን የመቀጠል እቅድ እንዳላት ያስታወቀችው መምህርት ነስረን አቡኤልፈዴል፤ በርእደ መሬቱ የፈረሰውን የአዳሴክ ትምህርት ቤት ምንግስት መልሱ እንደሚገነባው ተስፋ አደርጋለሁ ብላለች።
በሞሮኮ በሳለፍነው ሳምንት በደረሰውን ከባድ ርእደ መሬት ተከትሎ 530 የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ እና በከፊል የወደሙ ሲሆን፤ ርእደ መሬቱ ባለባቸው አካባቢ ትምርት መቋረጡም ተነግሯል።