የሞሮኮ መንግስት የሀገር ውስጥ የምግብ ዋጋ ከፍተኛ ሆኖ ስለ ወጪ ንግድ ማውራት አይቻልም ብሏል
ሞሮኮ የቲማቲም ምርት ወደ ውጭ ሀገራት እንዳይላክ አገደች።
ሞሮኮ ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ ቲማቲም ወደ ውጭ መላክን ገድባለች።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግን የቲማቲምን የሀገር ውስጥ ዋጋን ለመቀነስ ጠቅላላ እገዳ ተጥሎባታል ሲሉ የሀገሪቱ ዋና የአትክልትና ፍራፍሬ ላኪዎች ቡድን መሪ አስታውቀዋል።
የሞሮኮ ፍራፍሬ እና አትክልት ላኪዎች ፌዴሬሽን ኃላፊ ላሆሲን አዴርዶር ለሮይተርስ እንደተናገሩት የግብርና ሚንስቴር ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ከመከልከሉ በፊት በኮታ ለመላክ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ኃላፊው አርብ እለት ለላኪዎች የ1000 ቶን ኮታ ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም ይህ ከቀድሞው 1500 ቶን ያነሰ ነው ብለዋል።
በሞሮኮ እና በስፔን የተከሰተው መጥፎ የአየር ንብረት በዚህ ዓመት የአትክልት ምርትን በማስተጓጎሉ በአውሮፓ ውስጥ የሰላጣ ምግቦች እጥረት እና የዩናይትድ ኪንግደም የዋጋ ግሽበትን ከፍ እንዲል አድርጓል ነው የተባለው።
ነጋዴዎች የውጭ ገበያ ቅነሳው በአውሮፓ ህብረት እና በብሪታንያ የገበያ ድርሻቸውን እንደሚነካው ፈርተዋል።
"የረጅም ጊዜ የአቅርቦት ውልን ማክበር እየተሳነን ነው" ያሉት አንድ ነጋዴ፣ ከብሪታንያ ደንበኞች ጋር የሚደረጉ ውሎች አብዛኛዎቹ የሚፈረሙት በቋሚ ዋጋ ከአንድ ዓመት በፊት መሆኑን ጠቁመዋል።
"ሞሮኮ ለአውሮፓ ህብረት እና ለእንግሊዝ ገበያ በተረጋጋ የቲማቲም አቅራቢነት ያላት ስም አደጋ ላይ ነው" ብለዋል ።
የሞሮኮ መንግስት ቃል አቀባይ የሀገር ውስጥ የምግብ ዋጋ ከፍተኛ ሆኖ ስለ ወጪ ንግድ ማውራት አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል።
የሀገሪቱ የምግብ የዋጋ ግሽበት ከ1980ዎቹ ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሏል።