የሰሜን ኮሪያ ፕሬዘዳንት ለአባቴ ልደት አበባ አላደረሳችሁም በሚል አትክልተኞችን አሰሩ
አትክልተኞቹ የስድስት ወራት እስር ተፈርዶባቸው ዘብጥያ ወርደዋል
ሰሜን ኮሪያዊያን በየዓመቱ የቀድሞውን ፕሬዘዳንት ሞት ምክንያት ለቀናት መሳቅ እና አልኮል መጠጣት አይፈቀድላቸውም
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዘዳንት ለአባቴ ልደት አበባ አላደረሳችሁም በሚል አትክልተኞችን ማስራቸው ተገጿል፡፡
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዘዳንት ኪም ጆንግ ኡን አትክልተኞች አበባ ለአባታቸው ልደት ባለማድረሳቸው ለእስር ተዳርገዋል ሲል ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
የቀድሞው የሰሜን ኮሪያ ፕሬዘዳንት ኪም ጆንግ ሁለተኛ በ69 ዓመታቸው ከስምንት ዓመት በፊት ነበር ህይወታቸው ያለፈው፡፡
በስልጣን ላይ ያሉት የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ኪም ጆንግ ኡን የአባታቸውን ልደት ለማክበር ሽር ጉድ ሲሉ ቆይተዋል፡፡
የቀድሞውን ፕሬዘዳንት የልደት በዓል ያሳምራሉ ከተባሉት ውስጥ አበባ አንዱ ቢሆንም አትክልተኞቹ አበባውን በተባለበት ጊዜ ማድረስ አለመቻላቸው ፕሬዘዳንት ኪም ጆንግ ኡንን አስቆጥቷል፡፡
አበባዎቹ ባለመድረሳቸው የተቆጡት ፕሬዘዳንት አለቃቸውን ጨምሮ አትክልተኞቹ እንዲታሰሩ አዘዋል፡፡
በፕሬዘዳንቱ ትዕዛዝ መሰረትም አትክልተኞቹ ለአበባዎቹ እንክብካቤ አላደረጉም፣ስራቸውን ረስተዋል እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተከሰው ከስድስት ወር ጀምሮ እንዲታሰሩ ተወስኖባቸዋል፡፡
የቀድሞው የሰሜን ኮሪያ ፕሬዘዳንት ኪም ጆንግ ሁለተኛ የልደት በዓል በሀገሪቱ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል ዋነኛው ነው፡፡
ሰሜን ኮሪያን ከፈርንጆቹ 1994 ጀምሮ እስከ 2011 ዓመት ድረስ ለ17 ዓመታት በፕሬዘዳንትነት ያገለገሉት ኪም ጆንግ ሁለተኛ ሶስተኛ ልጃቸው በሆኑት ኪም ጆንግ ኡን ተተክተዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዘዳንት ህይወታቸው ካለፈ 11 ዓመት ቢሆናቸውም ሰሜን ኮሪያዊያን በየ ዓመቱ የሞት መታሰቢያ ቀናቸውን በማስመልከት ለ11 ቀናት እንዲያዝኑ፣እንዳይስቁ እና አልኮል መጠጥ እንዳይጠጡ ይገደዳሉ፡፡