ርያን ይሰኛል የተባለለት ታዳጊው 3 ያህል ቀናትን በድንገት በገባበት ጉድጓድ ውስጥ ማሳለፉ ተነግሯል
ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ የገባው ሞሮኳዊ ታዳጊ ጉዳይ ዓለምን እያነጋገረ ነው፡፡
ርያን ይሰኛል የተባለለት የ5 ዓመቱ ታዳጊ ባሳለፍነው ማክሰኞ ነበር በድንገት ተንሸራቶ 32 ሜትር ጥልቀት ካለው ጉድጓድ ውስጥ የገባው፡፡
ሴፍሾን በተባለው የሃገሪቱ ክልል በሚገኘው የሰሜናዊ ኢግራም መንደር ነዋሪ የሆነውን ይህን ታዳጊ በህይወት ለመታደግ በርካቶች እየተረባረቡ ነው፡፡
የሰሜን አፍሪካዊቷ ሃገር መንግስትም ርያንን በህይወት ለመታደግ ጥድፊያ ላይ ነው፡፡ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን ጨምሮ የህክምና ባለሙያዎችን በአደጋው ስፍራ አሰማርቷል፡፡
ርያንን እናድን (#SaveRayane) በሚል ስም በተለያዩ የማህበረሰብ ትስስር ገጾች ዘመቻዎች እየተደረጉ ነው፡፡ የሃገሪቱን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጨምሮ የተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች ለጉዳዩ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እየሰጡትም ይገኛሉ፡፡ በርካቶችም በስፍራው ተገኝተው የህይወት አድን ጥረቱን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡
በጭንቅ ላይ የሚገኘውን ታዳጊ ለመታደግ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በገመድ ወደ ጉድጓዱ ዘልቀው ታዳጊውን ከተቻለ ለማውጣት ካልሆነ የምግብ እና ሌሎች ለመተንፈስ የሚያስችሉትን መሳሪያዎች ለማድረስ ጥረቶች ተደርገውም ነበር፤ ሆኖም ርያን አመቺ ስፍራ ላይ ባለመሆኑ በቀላሉ ያን ለማድረግ አልተቻለም፡፡
ታዳጊው ባለበት ትይዩ ወደ ታች በመቆፈር በቶሎ ለመድረስ ከትናንት ጠዋት ጀምሮ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ እስካሁንም ምንም እንኳን ጥረቱን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሙም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 22 ሜትር ገደማ ጥልቀት ያለው ጉድጓድን ለመቆፈር ተችሏል፡፡
ይህም ታዳጊውን ለመታደግ ያስችላል በሚል ትልቅ ተስፋ እንደተጣለበትም ነው የተነገረው፡፡