ሞሮኮ የ2030 የአለም ዋንጫን ለማስተናገድ የሚደረገውን ፉክክር ተቀላቀለች
ራባት ከስፔንና ፖርቹጋል ጋር በጥምረት ውድድሩን ለማዘጋጅት ነው ፉክክሩን የተቀላቀለችው
የመጀመሪያው የአለም ዋንጫ አዘጋጅ ኡራጓይም ከሶስት ሀገራት ጋር በመጣመር የ2030ውን የአለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርባለች
ሞሮኮ ከስፔን እና ፖርቹጋል ጋር በመጣመር ከሰባት አመት በኋላ የሚካሄደውን የአለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች።
የሀገሪቱ ንጉስ መሃመድ ስድስተኛ የፈረሙበት ማመልከቻዋም የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር (ካፍ) ስብሰባ ሲደረግ ተነቧል።
“ሞሮኮ ከስፔንና ፖርቹጋል ጋር በመሆን የ2030 የአለም ዋንጫን ለማስተናገድ የሚደረገውን ፉክክር ተቀላቅላለች” ይላል መግለጫው።
የሶስቱ ሀገራት ጥምረት አፍሪካ እና አውሮፓን ይበልጥ የሚያስተሳስር መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፥ ሀገራቱ የተለየ ድባብ የሚኖረውን የአለም ዋንጫ እንደሚያስተናግዱ ይጠቅሳል።
ስፔንና ፖርቹጋል ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ካለችው ዩክሬን ጋር በመጣመር የ2030ውን የአለም ዋንጫ ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላቸው በመስከረም ወር 2022 ገልጸው ነበር።
ሞሮኮ ሁለቱን ሀገራት መቀላቀሏን ተከትሎ የኬቭ ተሳትፎ ምን ይሆናል የሚለው ግን እስካሁን አልተገለጸም ብሏል አሶሼትድ ፕረስ።
የስፔን፣ ፖርቹጋል እና ሞሮኮ ተወካዮች በዛሬው እለት በሩዋንዳ ኪጋሊ ከሚያደርጉት ስብሰባ በኋላ በሚሰጡት መግለጫ የዩክሬን ጉዳይ ምላሽ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።
ሞሮኮ የ2026ቱን የአለም ዋንጫ የማዘጋጀት ጥያቄዋ ከአራት አመት በፊት ውድቅ መደረጉን ተከትሎ የ2030ውን ውድድር ከሀገራት ጋር በመጣመር ለማሰናዳት ፍላጎቷን ስትገልጽ ቆይታለች።
በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን የ2010ቱን የአለም ዋንጫ ለማስተናገድ ያደረገችው ጥረትም ሳይሳካላት መቅረቱ የሚታወስ ነው።
በኳታሩ የአለም ዋንጫ አራተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ራባት፥በዶሃ አፍሪካንም ሆነ የአረቡ አለምን ያኮራ ክህሎትን አሳይታለች።
ከአለም ዋንጫው ማግስትም በየካቲት ወር 2023 የፊፋ የክለቦች የአለም ዋንጫን ማስተናግዷ አይዘነጋም።
ከስፔን እና ፖርቹጋል ጋር በመጣመር የ2030ውን የአለም ዋንጫ ለማዘጋጀት በይፋ ፉክክሩን የተቀላቀለችው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር የአለም ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ ካስተናገደችው ኡራጓይ ብርቱ ፉክክር ይጠብቃታል።
የ1930ውን የአለም ዋንጫ ያዘጋጀችው ኡራጓይ ከአርጀንቲና፣ ቺሊ እና ፓራጓይ ጋር በመጣመር ከ100 አመት በኋላ ውድድሩን ለማስተናገድ ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ይጠበቃል።
ሳኡዲ አረቢያም ስማቸው ካልተጠቀሰ የደቡብ አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ጋር የአለም ዋንጫውን ለማዘጋጀት ጥያቄ ልታቀርብ እንደምትችል እየተነገረ ነው።
ከሶስት አመት በኋላ የሚካሄደውን የአለም ዋንጫ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋር እንደሚያዘጋጁት ይታወቃል።