በዩክሬን ከጀመረው ጦርነት ወዲህ ምዕራባዊያን የሩሲያን ዲፕሎማቶች ማባረር ደጋግመውታል
የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር 15 በዲፕሎማሲያዊ ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ያላቸውን የሩሲያ ኤምባሲ ሰራተኞች እንዳባረረ አሳውቋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው በአሁኑ ጊዜ 40 የሚሆኑ የሩስያ ዲፕሎማቶች በኦስሎ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። በመሆኑም ተባረሩት የተባሉ "ዲፕሎማቶች" ቁጥር ከአንድ ሦስተኛ በላይ ነው።
ባለፈው ዓመት ሞስኮ በዩክሬን ከጀመረችው ጦርነት ወዲህ ምዕራባዊያን የሩሲያን ዲፕሎማቶችን ሲያባርሩ የኖርዌይ እርምጃ የቅርብ ጊዜ ነው።
ኢስቶኒያ፣ ኔዘርላንድስ እና ኦስትሪያ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከሀገራቸው ማስወጣታቸው ይታወሳል።
ኖርዌይም በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2022 ሦስት ሩሲያውያንን ከሀገሯ አስወጥታለች።
የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አኒከን ሁይትፌልድት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ የሞስኮ የደህንነት ሰራተኞች ተግባራቸው "ለኖርዌይ ስጋት ነው" ብለዋል።
"እንቅስቃሴያቸውን በጊዜ ሂደት ተከታትለናል፤ ከዩክሬን ወረራ በኋላ አስጊ ተግባራቸው ይበልጥ ጨምሯል" ሲሉም አብራርተዋል።
የተባረሩት መኮንኖች በቅርቡ ኖርዌይን ለቀው መውጣት አለባቸው በሚል ማሳሰባቸውም ተነግሯል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሞስኮ ለእርምጃው አጻፋዊ ምላሽ ትሰጣለች ሲል መዛቱን የመንግስት የዜና ወኪል ዘግቧል።