ሩስያ ወደ ዩክሬን መዝመት ለሚፈልጉ የሞስኮ ነዋሪዎች 22 ሺህ ዶላር ጉርሻ መክፈል ጀመረች
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተጨማሪ 170 ሺህ ወታደሮች እንዲመለመሉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል
ዩክሬናውያን ጦሩን እንዲቀላቀሉ አስገዳጅ ህግ ያወጣችው ኬቭ በወር እስከ 30 ሺህ አዳዲስ ወታደሮችን እየመለመለች ነው
ሩስያ ጦሯን ለሚቀላቀሉ የሞስኮ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ያልነበር ከፍተኛ የምዝገባ ጉርሻ እየሰጠች መሆኑ ተነገረ።
የከተማዋ ነዋሪዎች ጦሩን ለመቀላቀል ሲመዘገቡ እስከ 22 ሺህ ዶላር ድረስ የቦነስ ክፍያ እንደሚሰጣቸው ነው የተሰማው።
የሞስኮ ከንቲባ ሰርጌ ሶቢያኒ የምዝገባ ክፍያው ለተገደበ ጊዜ የሚቆይ መሆኑን ያስታወቁ ሲሆን የከተማዋ አስተዳደር ጦሩን ለሚቀላቀሉ ነዋሪዎች 1.5 ሚሊየን ሩብል ወይም 22ሺ ዶላር እንደሚከፈላቸው አረጋግጠዋል፡፡
በዚህ የምዝገባ ሂደት ተጠቅመው የሚመዘገቡ ነዋሪዎች በጦሩ ውስጥ ለሚኖራቸው የመጀመርያ አመት አገልግሎት በአጠቃላይ 5.2 ሚሊየን ሩብል ወይም 59600 ዶላር እንደሚያገኝ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ አዳዲስ ወታደሮችን ለመመዝገብ በተጀመረው ዘመቻ ከምዝገባ የጉርሻ ክፍያ ባለፈ ወታደሮቹ በዩክሬን ሲዋጉ ጉዳት ቢደርስባቸው እንደ ጉዳት መጠናቸው ከ5 ሺህ እስከ 11 ሺህ ዶላር የሚከፈላቸው ሲሆን፥ በውጊያ ህይወታቸውን ለሚያጡ የወታደር ቤተሰቦች ደግሞ 34 ሺህ ዶላር ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡
ዩክሬንም ሆነች ሩሲያ በአሰገዳጅ ሁኔታዎች እና በማበረታቻ አዳዲስ ወታደሮችን ለመመልመል ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
እድሜው እና አካላዊ ሁኔታው የሚፈቅደለት ዩክሬናዊ በሙሉ ጦሩን እንዲቀላቀል አሰገዳጅ ህግ ያወጣቸው ኬቭ በወር እስከ 30 ሺህ አዳዲስ ወታደሮችን እየመለመለች ትገኛለች፡፡
ለውጭ ሀገራት ዜጎች ጭምር ጦሯን ተቀላቅለው ዩክሬንን እንዲዋጉ ጥሪ ያደረገችው ሞስኮ በበኩሏ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እና ክፍያዎችን በማስተዋወቅ ጦሯን ለማጠናከር ጥረት እያደረገች ነው፡፡
በተለያየ ጊዜ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ወቅት የኔፓል ፣ ግብጽ ፣ ኮንጎ ፣ አፍጋኒስታን እና ህንድ ዜጎች ከሩስያ ጦር ጋር ተሰልፈው እየተዋጉ ይገኛሉ፡፡
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሀገሪቱ መከላከያ ተጨማሪ 170ሺ ምልምሎችን እንዲመዘግብ አዘዋል፤ ይህም የሩስያን አጠቃላይ የወታደር ቁጥር 2.2 ሚሊየን የሚያደርሰው እንደሚሆን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በጦርነቱ የሞቱ ወታደሮች ቁጥርን በተመለከተ ሁለቱም ሀገራት የተዛቡ መረጃዎችን እንደሚያወጡ ሲነገር የምእራባውያን መገናኛ ብዙሀን በግንቦት እና ሰኔ ወር ቁጥራቸው እስከ 70 ሺ የሚጠጉ የሩስያ ወታደሮች ሙት እና ቁስለኛ መሆናቸውን ዘግበዋል፡፡
ከሩስያ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቁጥር ያለው ጦር የሚያዋጉት የዩክሬን ጦር አዛዦች በበኩላቸው አሁንም ተጨማሪ ወታደሮች በፍጥነት እንደሚያስፈልጋቸው በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡