አንድ ሶስተኛ የዩክሬን ዜጎች ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች ላይ በመደራደር ጦርነቱ እንዲቆም ይፈልጋሉ ተባለ
ለጦርነቱ በፍጥነት መቆም በግዛት ጉዳዮች መደራደር ዋነኛ አማራጭ እንደሆነ የሚያምኑ ዜጎች ቁጥር በሶስት እጥፍ ጨምሯል
ለ29 ወራት በዘለቀው ጦርነት ሩስያ 18 በመቶ የዩክሬን ግዛትን ተቆጣጥራለች
አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ወይም 32 በመቶ ዩክሬናውያን ጦርነቱን ለማቆም ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው አንዳንድ ግዛቶች ላይ መደራደር አዋጭ እንደሚሆን እምነት እንዳላቸው ተነገረ፡፡
የኬቭ አለም አቀፍ የማህበረሰብ ጥናት ኢንስትቲዩት ግንቦት ወር ላይ ባደረገው ጥናት አንድ ሶስተኛ ዩክሬናውያን ጦርነቱ በፍጥነት ይቆም ዘንድ በድንበር ጉዳዮች ላይ መደራደርን እንደሚመርጡ ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው የተወሰኑ ግዛቶች ላይ መስማማት አፋጣኝ ሰላም ለማስፈን መሰረት ነው ብለው የሚምኑ ሰዎች መጠን ከአንድ አመት በፊት ከነበረበት በ10 በመቶ ጨምሯል፡፡
የማህበረሰብ ጥናት ተቋሙ ባሰባሰበው የህዝብ አስተያየት ድምጽ የሰጡ ዜጎች በግዛት ጉዳዮች ላይ መግባባትን እንደሚፈልጉ ቁጥራዊ መረጃዎችን ይፋ ከማድረግ ባለፈ ፤ የትኛዎቹ አካባቢዎች እንዲሁም በምን አይነት መንገድ ስምምነት ላይ መደረስ እንደሚችል ዝርዝር ጉዳችን አላስቀመጠም፡፡
አንዳንድ ዜጎች ጦርነቱ አሁን ከሚገኝበት ደረጃ አንጻር በመነሳት ሌሎች የግዛት አካባቢዎችን ነጻ ማውጣት በይደር እንዲቆይ ፍላጎት እንዳላቸውም ሮይተርስ ዘግቧል
በአንጻሩ ሩሲያ የዩክሬንን መሬት በሀይል መውረሯ ተገቢ አይደለም ብለው የሚያምኑ እንዲሁም ጦርነቱ እንዲያበቃ ሩሲያ ህዝበ ውሳኔ ያደረገችባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ከዩክሬን መውጣት አለባት የሚል አመለካከት ያላቸው ዜጎች ቁጥር 55 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ኢንስትቲዩቱ አስታውቋል፡፡
29 ወራትን በተሻገረው ጦርነት እስካሁን ባለው በ2014 በድምጽ ውሳኔ የተጠቃለለችውን ክሪሚያን ጨምሮ ሞስኮ የዩክሬንን 18 በመቶ ግዛት ተቆጣጥራ ትገኛለች፡፡
የዩክሬን ጦር ከባላፈው አመት ጀምሮ በርካታ ስፍራዎችን የተቆጣጠረውን የሩሲያ ጦር በመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ጥረት ቢያደርግም እምብዛም ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡
በ2022 ሩስያ ዶኔስክ ፣ ሉሀንስክ ፣ ኬሪሶን እና ዛፖሮዢያ ክልሎችን ወደ ራሷ ማጠቃለሏ ይታወሳል፡፡
ሞስኮ ለኬቭ ባቀረበችው የጦርነት ማቆም ጥሪ ላይ የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አስተዳደር ለነዚህ ክልሎች የሩስያ አካልነት እውቅና እንዲሰጥ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች፡፡
ኬቭ በበኩሏ ሩሲያ ወደ ቀደመ ስፍራዋ ካልተመለሰች በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከሚታወቁ ከዩክሬን ግዛቶች ሙሉ ለሙሉ ካልወጣች የሚደረግ ድርድር እና የጦርነት ማቆም ስምምነት የለም በሚል አቋሟ ጸንታለች፡፡