ሩሲያ የዩክሬን ኔቶን መቀላቀል ምድርን ወደ ፍርስራሽነት የሚለውጥ ጦርነትን ያስከትላል ስትል አስጠነቀቀች
የቀድሞው የሩስያ ፕሬዝዳንት ሜድቬደቭ የኔቶ ተስፋፊነት ሩስያ የማትፈልገውን አማራጭ እንድትጠቀም እያስገደዳት ነው ብለዋል
የዩክሬን የኔቶ አባልነት በማይቀለበስበት ደረጃ ስለመድረሱ ባሳለፍነው ሳምንት መገለጹ አይዘነጋም
የቀድሞው የሩስያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ዩክሬን ኔቶን በአባልነት የመቀላቀል አጀንዳ ምድርን ወደ ፍርስራሽነት የሚለውጥ ጦርነትን የሚያስከትል ነው አሉ።
በሩስያ የደህንነት ምክር ቤት ምክትል ሰብሰባቢነት እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሜድቬዴቭ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት የኔቶ ተስፋፊነት እና ጠብ አጫሪነት ሩስያ የማትፈልገውን አማራጭ እንድትጠቀም እያስገደዳት ይገኛል ብለዋል።
ድርጅቱ ዩክሬንን በአባልነት የሚያቅፍ ከሆነ በሩስያ ላይ ይፋዊ ጦርነት እንደታወጀ ይቆጠራል ያሉት ሜድቬዴቭ፤ ኔቶ አውሮፓን እና በአጠቃላይ ምድርን ወደ ፍርስራሽነት የሚቀየር ጦርነት ለማስቆም ቢሞክር ብልህነት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት አመታዊ ጉባኤውን ያደረገው ባለ 32 አባላቱ ድርጅት ኔቶ ዩክሬን ስብስቡን የመቀላቀሏ ነገር ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ደርሷል ማለቱ ይታወሳል።
ይህ ማለት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኬቭ የኔቶ አባል መሆኗ አይቀርም እንደማለት ነው።
የሰሜን አትላንቲኩ ድርጅት ወደ ድንበሬ መጠጋት ያሰጋኛል ያለችው ሩስያ ዩክሬንን ከወጋችባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ቡድኑ ወደ ድንበሯ እየቀረበ መምጣትን ለመቀልብስ እንደሆነ ትናገራለች።
ይሁን እና ሞስኮ በኬቭ ላይ ስትዘምት ሌሎች ድንበር የሚጋሯት ሁለት ሀገራት በተፈጠረባቸው ስጋት ኔቶን መቀላቀላቸው ለሩስያ ያልተሰላ ኪሳራ ያስከተለ ነው የሚሉ የደህንነት ተንታኞች አሉ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሜድቬዴቭ እንዳሉትም ከሶቭየት ህብረት መፍረስ በኋላ ሩስያ እንደማንኛውም የአውሮፓ ሀገር መበልጸግ ፣ ወታደራዊ አቅሟን ማሳደግ እና በአለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሚናዋን ለመወጣት ጥረት ብታደርግም በኔቶ እና አባል ሀገራቱ ዘንድ በስጋትነት ከመታየት አልተረፈችም ነው ያሉት።
ለአመታት አሜሪካ እና ኔቶ ሩስያን በተቀናቃኝነት መዝግበው ጸረ ሞስኮ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር አሁን ደግሞ ወደ ድንበራችን እጅጉን እየተጠጉ ነው የዩክሬን የኔቶ አባልነት ደግሞ በምዕራባውያን እና በሩስያ መካከል ያለውን የሳሳ ግንኙነት በማይጠገን ሁኔታ የሚበጥስ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።