“ከህወሓት ጋር ለመነጋገር የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሟል” - ጠ/ሚ ዐቢይ
ሰላም ለማምጣት ያለመ ነው ያሉት ኮሚቴ በአቶ ደመቀ መኮንን እንደሚመራ ገልጸዋል
ከህወሓት ጋር ድርድር ሲጀመር ይፋ እናደርጋለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ
በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽ፤ ከህወሓት ጋር ለመደራደር ኮሚቴ ተቋቁሞ አስፈላጊ ሁኔታዎችን እየተያደረጉ ነውም ብለዋል፡፡
የም/ቤቱ አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አሁን ላይ ድርድርን አስመልክቶ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ሕዝቡ ይህንን ማወቅ እንዳለበትና የአማራ ክልል እና የኤርትራ መንግስትም በዚህ መሳተፍ እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡
ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ሰላምን ለማምጣት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከህወሃት ጋር ወደ ጦርነት የተገባው በይፋ ነው ድርድሩም የሚካሄደው በይፋ ነው” ብለዋል፡፡
“ህወሓት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ጠላት“ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላምን ለማምጣት “የምንደብቅበት ምክንያት የለም” ብለዋል፡፡
ከህወሓት ጋር ንግግር ሲጀመር ይፋ እንደሚደረግ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኮሚቴው ያዘጋጀውን በሚመለከት በሁለት ሳምንት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡
“ከህወሓት ጋር ድርድር የሚደረገው የምንፈልጋቸው ሲሟሉ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመንግስት ወገን ሰላም ስለተፈለገ ብቻ ግን ሰላም ሊመጣ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በናይጀሪያ ቆይታቸው ከህወሃት አመራሮች ጋር መገናኘታቸውን አስመልክቶ ስለተሰራጨው መረጃ “በናይጀሪያ ቆይታዬ ለአንዲት ሰከንድ ስለ ህወሓት አልተነሳም” ብለዋል፡፡
የጸጥታ ተቋማት ለህወሓት ብቻ እንደማይዘጋጁ ገልጸው፤ ጦሩ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቁጥር፣ በስልጠና እና በቴክኖሎጂ ከህወሓት ኃይል ሁለት ሶስት እጥፍ የበለጠ ሀይል በተሻለ መንገድ መገንባቱንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የተጀመረው ጦርነት በአካል እና በሳይበር በመሆኑ ያንን የሚመጥን ሰራዊት እየተገነባ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ ላይ 5 ሺህ 860 የሳይበር ጥቃት ተፈጽሟል ያሉም ሲሆን ጥቃቱ በሚሊዮን ያጣንበት በቢሊዮን ያተረፍንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ህግ የማስከበር ስራው በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች በመካሄድ ላይ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በኦሮሚያ፣በአማራ፣ አዲስ አበባ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተሻለ ስራ መሰራቱን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፤ በኦሮሚያ ክልል በተወሰደው እርምጃ ከ1 ሺህ በላይ የሸኔ ወታደሮች መገደላቸውንበመጠቆም፡፡
ህግ የማስከበር ስራው እየተሰራ ያለው ከህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት መሰረት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በህወሓት አስተዳደር የትግራይ ሕዝብ ያተረፈው ጥላቻን እንደሆነ ገልጸው አሁንም ችግርና ስደት እንዳለና አመራሮቹ የራሳቸውን ኑሮ የተሻለ ሊያደርጉ ቢችሉም ለሕዝቡ እንዳልሰሩ ገልጸዋል፡፡