መንግስት ከህወሃት ጋር ድርድር የሚካሄድበትን ቦታ ለመወሰን ከአፍሪካ ህብረት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታወቀ
ኮሚቴው ዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል
በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት ለማቅረብ “አስፈላጊ ቅደም ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው” ብሏል ኮሜቴው
የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሃት ጋር አካሂደዋለሁ ያለው የሰላም ንግግሩ የሚካሄድበትን ቦታ እና ጊዜ ለመወሰን ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
መንግስት “አሸባሪ” ብሎ ከፈረጀው ህወሃት ጋር የሰላም ንግግር እንደሚያደርግ ቀደም ብሎ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን ለዚህ የሚሆን ቡድንም ማቋቋሙን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
መንግስት “የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ” ብሎ የሰየመው ተደራዳሪ ቡድን ዛሬ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው ይህ ተደራዳሪ ቡድን እስካሁን የነበረውን እንቅስቃሴ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ውይይት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት ለሰላም ዕድል ለመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ እንደቆየ የገለጸው ተደራዳሪ ቡድኑ የተናጠል የሰብዓዊነት ተኩስ አቁም ማወጅን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማንሳትን፣ እስረኞች መፍታትን፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ማሳደግን ለአብነት ጠቅሷል፡፡
የሰላም ንግግር ያለቅድመ ሁኔታ በየተኛውም ቦታ እና ጊዜ ለመጀመር መንግስት አሁንም ዝግጁነት እንደሆነ ገልጿል፡፡ በዚሁ መሰረት የሰላም አማራጭን በዘላቂነት እውን ለማድረግ እና የግጭት ሰለባ እና ተጋላጭ በሆኑ የትግራይ፣ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ ዜጎች በዕለት ከዕለት ኑሮዋችው እየገጠማቸው ያለውን ችግር መቀረፍ እንደሚገባ “ትኩረት ሰጥቼ ተወያይቻለሁ” ብሏል፡፡
የተደራዳሪ ቡድን ኮሚቴው፤ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማድረስ፤ የመሰረተ ልማት እና የመሰረታዊ አገልግሎቶች በፍጥነት ስራ በሚጀምሩበት ሁኔታ፤ በአጭር ጊዜ ላይ የተኩስ አቁም እንዲኖር ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ውይይት ማድረጉን ገልጿል፡፡
ኮሚቴው ሂደቱን ለማፋጠን ይረዳ ዘንድ፣ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እና ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶች መሰረት የሚጥል “የሰላም ምክረ ሃሳብ” ላይ ውይይት በማድረግ የምክረ ሃሳብ ሰነዱን መጽደቁ አስታውቋል፡፡
ኮሚቴው ያጸደቀውን ምክረ ሃሳብ ለአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ወኪል እንዲቀርብ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የአፍሪካ ህብረትን የሰላም ጥረት በሚደግፉ አካላት ትብብር በመታገዝ በአጭር ጊዜ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ይቻል ዘንድ፣ የሰላም ምክረ ሃሳቡን በተመለከተ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተወስኗል ብሏል ኮሜቴው፡፡
በተጨማሪም ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሲገባ በሚፈጠረው ሁኔታ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በተቻለ ፍጥነት መልሶ ማቅረብ ይቻል ዘንድ፣ አስፈላጊ ቅደም ዝግጅቶች መደረጋቸውን ኮሜቴው ገልጿል፡፡
የድርድር ቡድኑ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ከአፍሪካ ህብረት ጎን በመቆም የሰላም ጥረቱ የተሳካ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋትፅዖ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርቧል።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በተናጠል በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በድርድር ለመቋጨት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡
መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ከህወሓት ጋር ለመደራደር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ቡድን መቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በቀረቡበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል
ህወሓት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው ለመደራደር መፈለጉን ከመግለጻቸው ቀደም ሲል በኬንያ አስተናጋጅነት እና አመቻችነት ለሚደረገው ድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልፆ ነበር፡፡መንግስት ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ብቻ ይመራ ሲል ህወሓት ግን በዚህ እንደማይስማማ ገልጿል፡፡