አብዛኞቹ አሜሪካውያን ሀገራቸው አለማቀፍ መሪነቷ እንዲያድግና የመከላከያ በጀቷ እንዲጨምር ይፈልጋሉ - ጥናት
57 በመቶ አሜሪካውያን ዋሽንግተን በአለም አቀፍ ጂኦፖለቲካዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲኖራት ይፈልጋሉ ተብሏል
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ቅድሚያ ለአሜሪካ" በሚለው መርሀቸው በሀገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር እቅድ አላቸው
አብዛኛዎቹ አሜሪካውያን ዜጎች ሀገራቸው በአለም አቀፍ ጉዳዮች ያላት መሪነቷ እንዲያድግ እና የመከላከያ ወጪ እንዲጨምር እንደሚፈልጉ ከህዝብ የተሰበሰበ አስተያየት አመላከተ፡፡
ምንም እንኳን አሜሪካውያን ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጀምሮ እስከ ደቡባዊ የአሜሪካ ድንበር ጥበቃ ድረስ በሀገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ፕሬዝዳንት ቢመርጡም፤ በጥናቱ ከተካተቱት ውስጥ 57 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካ በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ግንባር ቀደም ሆና ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ይህ ቁጥር ባለፈው አመት ከነበረው 42 በመቶ ጋር ሲነፃፀር የ15 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡
“ዘ ሬገን ብሔራዊ መከላከያ ጥናት ማዕከል” በሰበሰበው የህዝብ አስተያየት ላይ 80 በመቶ ዜጎች አሜሪካ የመከላከያ በጀቷን እንድታሳድግ ፍላጎት አላቸው ብሏል፡፡
ነጻነትን ማሳደግ 61 በመቶ እንዲሁም የአለም አቀፍ ድጋፍ እንዲደረግ እንደሚደግፉ ድምጻቸውን ከሰጡ 43 በመቶ ዜጎች ጋር ሲወዳደር ለመከላከያ በጀት እንዲጨመር የጠየቁ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ብልጫ አሳይቷል፡፡
የጥናቱ አማካሪ ቦርድ አባል እና የማዕከሉ ዳይሬክተር የሆኑት ብራድሊ ቦውማን ለአሜሪካ ድምጽ እንደተናገሩት፤ አብዛኛዎቹ ምላሽ ሰጪዎች አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን የጦር መሳርያ ድጋፍ እንድትቀጥል እና ኬቭ በሩስያ ውስጥ የአሜሪካ ሚሳኤሎችን እንድትተኮስ መፍቀድን ይደግፋሉ፡፡
ሆኖም በጦር መሳርያ ድጋፍ አሰጣጡ ላይ በሁለቱ ፓርቲ ደጋፊዎች መካከል ልዩነት አለ፤ 74 በመቶ የዴሞክራት ደጋፊዎች የጦር መሳርያ እገዛ መቀጠልን ሲደግፉ በአንጻሩ ከሪፐብሊካን ደጋፊዎች ከዚህ ሀሳብ ጎን የቆሙት 42 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው፡፡
በተጨማሪም 60 በመቶ ዜጎች ምንም እንኳን ዩክሬን አንዳንድ ግዛቶቿን አሳልፋ መስጠት ቢኖርባትም ግጭቱ በሰላም ድርድር ያበቃል ብለው ያምናሉ፡፡
እስራኤልን በተመለከተ 54 በመቶዎቹ የጦር መሳርያ እገዛው እንዲቀጥል ሲፈልጉ፤ የጦርነቱን መቀጠል እና የተኩስ አቁም ተደርጎ ግጭቱ እንዲቋጭ የሚሹት ደግሞ በ45 በመቶ ድምጽ እኩል ሆነዋል፡፡
በጥናቱ ከተካተቱት ውስጥ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ቻይና ታይዋንን ከወረረች አሜሪካ ለታይዋን ይፋዊ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የጠየቁ ሲሆን ፤ ሁለት ሶስተኛው ደግሞ ዋሽንግተን በቤጂንግ ላይ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ በማድረግ ምላሽ እንድትሰጥ የሚፈልጉ ናቸው፡፡