አሜሪካ ዩክሬን የግዳጅ ወታደራዊ መመልመያ እድሜን እንድትቀንስ አሳሰበች
ዩክሬን በበኩሏ ተጨማሪ ወታደሮችን የማስታጥቃቸው የጦር መሳሪያ የለኝም ብላለች
የዩክሬን ዋነኛ ችግር በጦር ግምባር ያሉ ወታደሮችን የሚተካ አዲስ ወታደር አለመኖር እንደሆነ አሜሪካ ገልጻለች
አሜሪካ ዩክሬን የግዳጅ ወታደራዊ መመልመያ እድሜን እንድትቀንስ አሳሰበች፡፡
አንድ ሺህ ቀን ያለፈው የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት በርካታ አዳዲስ ነገሮችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስልጣን ከማስረከባቸው በፊት ዩክሬንን ማስታጠቅ እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የሩሲያ ጦር ከመቼውም ጊዜ በላይ በየቀኑ የሚቆጣጠራቸው ቦታዎች እያደገ ሲሆን ዩክሬን ደግሞ ተጨማሪ የረጅም ርቀት ጦር መሳሪያ እንዲሰጣት በመወትወት ላይ ናት፡፡
ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ዩክሬን በግዳጅ የምትመለምላቸውን ወታደሮች ቁጥር እንድታሳድግ አሳስበዋል፡፡
አሁን ላይ ዩክሬን የግዴታ ወታደራዊ አገልግሎት የጣለችው እድሜያቸው ከ25 ዓመት እና ከዛ በላይ በሆኑ ዜጎቿ ላይ ነው፡፡
እኝህ የአሜሪካ ባለስልጣን የግዳጅ ወታደራዊ መመልመያ ዝቅተኛ የእድሜ ጣሪያን ከ25 ወደ 18 ዝቅ እንድታደርግ ጠይቀዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ከሩሲያ ጦር ጋር እየተዋጉ ያሉ የዩክሬን ወታደሮችን እረፍት እንዲያደርጉ፣ እንዲያገግሙ እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ አዲስ ወታደሮች ከወዲሁ መመልመል ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
የዩክሬ በበኩሏ አሁን ላይ ያለብን ችግር የጦር መሳሪያ እንጂ የተዋጊዎች አይደለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
አዲስ ወታደሮችን ለመመልመል ተጨማሪ የጦር መሳሪያ እና ተያያዥ ቁሳቁሶች ድጋፍ ያስፈልጋል ያለችው ዩክሬን በተለይም መሀል ሩሲያን መምታት የሚያስችለኝ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ጠይቃለች፡፡