በ2022 በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉ የይለፍ ቃላት የትኞቹ ናቸው?
ጠንካራ የይለፍ ቃላት መጠቀም ተደጋግሞ ቢመከርም አሁንም “123456” የሚል ፓስወርድ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም
አጫጭር እና ተገማች የሆኑ የሀገራት፣ የከተሞችና የታዋቂ ሰዎችን ስም የይለፍ ቃል ማድረግም እየተለመደ መጥቷል ተብሏል
ማስጠንቀቂያው ቢቀጥልም አሁንም በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚጠቀሟቸው የይለፍ ቃላት (ፓስወርድ) በቀላሉ ተገማች እና ተመሳሳይ ናቸው ተባለ።
የይለፍ ቃላት ሚስጢራዊና ማንም ሰው ሊገምታቸው የማይችሉ መሆን ቢገባቸውም ብዙ ሰዎች ሊታወሱና በቀላሉ ሊታወቁ የሚችሉ ፓስወርዶችን ይጠቀማል።
ስፔኮሶፍት የተሰኘው የይለፍ ቃላት አማካሪ ተቋም ይፋ ያደረገው አዲስ ጥናትም ይሄው ችግር መቀጠሉን አሳይቷል።
ከ800 ሚሊየን በላይ በመረጃ መንታፊዎች እጅ የወደቁ የይለፍ ቃላት ላይ ጥናት ያደረገው ተቋሙ፥ 88 ከመቶው የይለፍ ቃላት ከ12 ፊደላት ወይም ቁጥሮች ያነሱ መሆናቸውን አመላክቷል።
አብዛኞቹ ተደጋግመው ጥቅም ላይ የዋሉ የይለፍ ቃላትም 'password'፣ 'admin'፣ 'welcome' እና 'p@ssw0rd' መሆናቸውን ነው ስፔኮሶፍት ይፋ ያደረገው።
- በ6 ወራት በኢትዮጵያ ላይ ከ2000 በላይ የሳይበር ጥቃቶችና ሙከራዎች ተደርገዋል- ኢንሳ
- በኢሜል ከሚፈጸም የመረጃ ምንተፋ (ፊሺንግ) ራሳችን እንዴት እንጠብቅ?
ሳይበር ኒውስ መረጃ ዘራፊዎች ይፋ ባደረጓቸው ከ56 ሚሊየን በላይ የይለፍ ቃላት ላይ ባደረገው ጥናትም ቀላል የይለፍ ቃላትን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር አሁንም ከፍተኛ መሆኑን አመላክቷል።
በ2022 ለጥቃት ከተጋለጡ የኢሜል አድራሻዎች ውስጥ “123456”ን የይለፍ ቃል አድርገው የተጠቀሙ ሰዎች ቁጥር 111 ሺህ 417 መሆኑም እጅግ አሳሳቢ ነው ብሏል ሳይበር ኒውስ።
ባለፈው አመት የግዙፉ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኒቪዳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች የይለፍ ቃላት ተሰርቆ ይፋ ተደርጎ ነበር።
አብዛኞቹ የይለፍ ቃላት የተሰበረባቸው ሰዎች የሚጠቀሟቸው የይለፍ ቃላትም እንደ 'Nvidia'፣ 'qwerty' እና 'nvidia3d' ያሉ መሆናቸው የቴክኖሎጂ ኩባንያውን ሰራተኞች ትዝብት ላይ መጣሉ አይዘነጋም።
የተቋማትን ኮምፒውተሮች የሚጠቀሙ ሰራተኞች የተለመዱ የይለፍ ቃላትን የመጠቀም ልማዳቸው ለጥቃት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል።
የታዋቂ ሰዎችን፣ የሀገራትን እና ከተሞችን ስም ብቻ የይለፍ ቃል የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑንም የሳይበር ኒውስ ጥናት ያሳያል።
የኮሎምቢያዋ ካሊ እና የፔሩ መዲናዋ ሊማ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሆነው ቀርበዋል።
ኦማን፣ ማሊ እና ህንድም በርካቶች የይለፍ ቃል ያደረጓቸው ሀገራት ስም ሆኖ ተገኝቷል።
ስፔኮሶፍት ያወጣው ጥናት ከ12 በላይ ፊደላት፣ ቁጥሮችና ምልክቶችን ያካተቱ የይለፍ ቃላት ጭምር ከመረጃ መንታፊዎች አለማምለጣቸውን የሚያሳይ ነው።
በመሆኑም ጠንካራ የይለፍ ቃላትን መጠቀም እንዳለ ሆኖ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ሌሎች የይለፍ ቃላት መጠበቂያ መንገዶችን መከተል እንዳለባቸው ነው ያሳሰበው።