የዓለማችን ጀግና እናቶች እነማን ናቸው?
የእርስዎ ጀግና እናት ማን ነች?
የእናቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር ከጀመረ 120 ዓመት ሊሞላው ጥቂት ዓመት ብቻ ቀርቶታል
የመንግስታቱ ድርጅት በየዓመቱ በፈረንጆች ግንቦት 14 የእናቶች ቀን ሆኖ እንዲውል በወሰነው መሰረት እለቱ ይከበራል።
እናቶች ለዓለማችን የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማስታወስ በሚል ከፈረንጆቹ ከ1907 ጀምሮ በየዓመቱ በመከበር ላይ ነው።
እናትነት በራሱ ጀግንነት ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈተናዎችን ተቋቁመው ለየት ያሉ ስራ የሰሩ እናቶች ደግሞ ይኖራሉ።
በዓለማችን በየቦታው ለልጆቻቸው እና ለዓለማችን እልፍ መልካም ስራዎችን ያበረከቱ እልፍ እናቶች ቢኖሩም በዚህ ዘገባችን ግን ጥቂቶቹን ብቻ እናነሳለን።
ሜሪ ኩሪ (1867-1934) የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሜሪ ኩሪ በአደጋ ምክንያት ባሏን ብታጣም ሁለት ልጆቿን ከማሳደግ ጎን ለጎን በኬሚስትሪ ዘርፍ በሰራችው ምርምር የኖቤል ሽልማትን ማግኘት ችላለች።
ሁለተኛዋ የዓለማችን ጀግና እናት በመባል የምትታወቀው ሳጁርነር ትሩዝ ስትሆን በባርነት የተሸጠው የአምስት ዓመት ወንድ ልጇን ከባርነት ለማስለቀቅ ባደረገችው ተጋድሎ ጀግና ተብላለች።
ሶስተኛዋ የአለማችን ጀግና ካቲ ሂድብ ስትሆን ወላጅ አልባ ህጻናትን ለመርዳት ባደረጉት ጥረት ይታወሳሉ።
ይህች እናት በተለይም በዚምባብዌ፣ ህንድ፣ ቦስኒያ፣ ሜክሲኮ፣ ቦሊቪያ እና ዩጋንዳ ወላጅ የሌላቸውን ህጻናት በማሳደግ የዓለማችን ባለውለታ እንደሆኑ ተገልጿል።
ሶማሊያዊቷ ዋሪስ ድሬ ሌላኛዋ የዓለማችን ጀግና እናት የተባለች ሲሆን በተለይም በ13 ዓመቷ የህጻንነት እድሜዋ የቀረበላትን ጋብቻ በመሸሽ ያሳለፈቻቸው ውጣ ውረዶች ከባድ ነበሩ ተብሏል።
ብዙ አስቸጋሪ የህይወት ምዕራፎችን በማለፍም ስኬታማ ሞዴል ለመሆን የበቃች ሲሆን በዓለም ላይ ያለእድሜ ጋብቻን እና የሴት ልጅ ግርዛትን የሚያስቀሩ ስራዎችን ማከናወኗ ተገልጿል።
የዓለማችን የመጀመሪያዋ በጥረቷ ሚሊየነር የሆነችው ጥቁር ሴት ሳራህ ብሪድላቭ ሌላኛዋ የምድራችን ጀግና እናት ተብላለች።
ይህች እናት የባሪያ ንግድ ሰለባ የነበረች ሲሆን የወደፊት ህይወቴ የባሰ አስቀያሚ ሳይሆን ከድህነት መውጣት አለብኝ፣ ለልጆቼም የተሻለ ሁኔታ መፍጠርም አለብኝ በሚል ወደ ንግድ ገብታ በጥረቷ እና በላቧ ስኬታማ በመባል የብዙ እናቶች አርዓያ መሆኗ ተገልጿል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከ2 ሺህ 500 በላይ አይሁዳዊያንን ከእልቂት የታደጉት ፖላንዳዊቷ ኢሬና ሴንድለር ደግሞ ተጨማሪ የዓለማችን ጀግና እናት ተብለዋል።
አይሁዳዊያንን ከናዚ እልቂት የታደጉት እኝህ እናት ድርጊታቸው መታወቁን ተከትሎ ብዙ መከራን የተቀበሉ እና እንዲገደሉ ቢፈረድባቸው በተዓምር ከሞት ተርፈው በፖላንድ መንግሥት የጀግና ሜዳሊያ ለመሸለም በቅተዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለማችን ብዙ ጀግና እናቶችን መጥቀስ ቢቻልም ለእርስዎ ጀግና እናት ማን ናት? ጀግና እናት ማለትስ ለእርስዎ ምን ማለት ነው? አስተያየትዎን ያካፍሉን።
መልካም የእናቶች ቀን!!