በሞዛምቢክ ግጭት አንድ ሚሊዮን ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል
የሞዛምቢክ መንግስት ጽንፈኛ የሽብር ቡድን መሪ በጦሩ መገደሉን አስታውቋል።
ቡድኑ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ከሚዋጋዊ እስላማዊ መንግስት ጋር ግንኙነት አለው ተብሏል።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚንስቴር እንዳለው ቦኖሜድ መችዱ ወይም ኢብን ኦማር የተባለው ግለሰብ ሸማቂ ቡድኑን ከ2017 ጀምሮ ሲመራ ነበር።
ሚንስቴሩ በመግለጫው መሪው ከሁለት የቡድኑ ከፍተኛ አዛዦች ጋር መገደሉን ገልጿል።
ኢብን ኦማርና ሌሎች ከእስላማዊ መንግስት ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች፤ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር በተደረገ ተልዕኮ ነው ተገደሉ የተባሉት።
ቢቢሲ በዘገባው በገለልተኝነት ግድያውን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ጠቅሷል።
ከሁለት ዓመት በፊት አሜሪካ ኦማርን የሽብር ቡድኑ መሪ መሆኑን አሳውቃለች። በካቦ ዴልጋቶ ግዛት ለደረሰውና በፓልማ ሆቴል ለብዙዎች ሞት ምክንያት ለሆነው ጥቃት ተጠያቂ አድርጋለች።
ከሩዋንዳና ከሌሎች የደቡብ አፍሪካ ሀገራት ጋር በመሆን የሞዛምቢክ መንግስት የሽብር ቡድኖች ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ከፍቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሞዛምቢክ ብጥብጥ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ግጭቱ የበርካታ ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ፕሮጀክትን አስተጓጉሏል።