ኢትዮጵያ ከብሪታንያ ጋር ሽብርተኝነትን ለመከላከል የ12 ሚሊዮን ዶላር ሰምምነት ተፈራረመች
ስምምነቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ እና ሶማሊያን ያካትታል ተብሏል
ስምምነቱ ሀገራቱ ሽብርተኝነትን መዋጋት የሚያስችሉ የድንበር ላይ ቁጥጥር ስራዎችን ለመስራት እንደሚያግዝ ተገልጿል
ብሪታንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሶስት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር ሽብርተኝነትን መከላከል ያለመ ስምምነትን ተፈራርማለች።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ይህ ስምምነት 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተመደበለት ሲሆን፤ ሀገራቱ በጋራ ሽብርተኝትን እንዲከላከሉ ያግዛል።
በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ያግዛል የተባለው ይህ ስምምነት በተለይም ሀገራቱ በድንበሮች አካባቢ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር እንዲያደርጉ ያግዛል ተብሏል።
የብሪታንያ ደህንነት ሚኒስትር ቶም ቱገንዳት ለቢቢሲ እንዳሉት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በሚደረግላቸው ድጋፍ የሽብርተኝነት መከላከያ ፖሊሲዎችን እና አሰራሮችን እንዲቀርጹ ይረዳቸዋል ብለዋል።
ብሪታንያ በሽብርተኝነት ጉዳይ ከሶስቱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር እንዲህ አይነት የበጀት ድጋፍ ስታደርግ የመጀመሪያዋ ነው የተባለ ሲሆን በበጀት ድጋፉ በድንበሮቻቸው አካባቢ ያለውን የደህንነት ስጋት እንዲቆጣጠሩ ያደርጋል ተብሏል።
የሶስቱ ሀገራት የድንበር አካባቢዎች ጥብቅ ቁጥጥር አይደረግባቸውም የተባለ ሲሆን ቴክኖሎጂ እና የሰለጠነ የሰው ሀይል ደግሞ ድንበሮቹን መቆጣጠር እንዳይችሉ ያደረጉ ምክንያቶች እንደነበሩ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ለቁጥጥር አስቸጋሪ ናቸው የተባሉ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የድንበር አካባቢዎች ላይ ውጤታማ የአስተዳድር ስርዓት አለመዘርጋታቸው ለደህንነት ስጋቱ ሌላኛው ምክንያት ነውም ተብሏል።
በነዚህ ምክንያቶችም አልሻባብ እና ሌሎች የሽብር ቡድኖች ጥቃቶችን እንዲያደርሱ አድርጓል ያሉት የብሪታንያ ደህንነት ሚኒስትር ብሪታንያ በምታደርገው ድጋፍ መሰረት በድንበሮች አካባቢ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የጸጥታ ስራዎችን መስራት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።