ልዩ የስራ ጠባይ ላላቸው የይለፍ ፍቃድ ይሰጣል ተባለ
ከስራቸዉ ፀባይ አንፃር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣በደንቡ ወይም በአፈፃፀም መመሪያዉ በተገለፁት ጉዳዮች ላይ በቀጥታ የሚሳተፉ ሰዎችም ፍቃዱን ያገኛሉ
ከጤና ባለሙያዎች፣ ከሚዲያ አካላትና ከሌሎችም ጥያቄ እየቀረበ ነውም ተብሏል
ልዩ የስራ ጠባይ ላላቸው የይለፍ ፍቃድ ይሰጣል ተባለ
ከኮድ-2 ተሽከርካሪዎች የፈረቃ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ልዩ የስራ ጠባይ ያላቸው አካላት በልዩ የተሽከርካሪ የይለፍ ፍቃድ እንደሚንቀሳቀሱ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ እንዲተገበር ሆኖ ከወጣው የፈረቃ እንቅስቃሴ መመሪያ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ያላቸው አካላት ወደ ባለስልጣኑ እየመጡ ነው ያሉት የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይግዛው ዳኘው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተቀመጠው የግል ወይም የቤት ተሽከርካሪዎች አጠቃቀም መመሪያ መሰረት እንደሚስተናገዱ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ከጤና እና ከፋርማሲ ባለሙያዎች፣ ከሚዲያ አካላት፣ከአካል ጉዳተኞች እና ከሌሎች አካላትም የፍቃድ ጥያቄ ለባለስልጣኑ እየቀረበ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
በመመሪያው አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት ይስተናገዳሉ ያሉም ሲሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና አዋጁን የተመለከቱ ጉዳዮችን ለማስፈጸም በወጣው ደንብና መመሪያ ላይ በቀጥታ የሚሳተፉ አካላት ከባለስልጣኑ በሚሰጣቸው ልዩ የይለፍ ፍቃድ ብቻ እንደሚንቀሳቀሱም ገልጸዋል፡፡
ኮድ-2 የቤት ተሽከርካሪዎች ከዛሬ እለተ ሰኞ ሚያዚያ 12 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ በሰሌዳ ቁጥር ሙሉና ጎዶሎነት በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም መሰረት የሰሌዳ ቁጥራቸው መጨረሻ ጎዶሎ የሆነ ተሽከርካሪዎች ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ መንቀሳቀስ የሚችሉ ሲሆን የሰሌዳቸው የመጨረሻ ቁጥር ሙሉ ወይም ዜሮ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ማክሰኞ፣ ሀሙስ እና ቅዳሜ ይንቀሳቀሳሉ፡፡
እሁድ እለት ደግሞ ሁሉም ተሽከርካሪዎች እንዲንቀሳቀሱ ተፈቅዶላቸዋል።