የሙርሌ ታጣቂዎቸ የኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው በጋምቤላ ክልል ጥቃት ማድረሳቸውን ክልሉ አስታወቀ
በጥቃቱ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል ተብለዋል
የሙርሌ ታጣቂዎች ባለፈው ወር በንጹሃን ላይ ጥቃት ማድረሳቸውና የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል
ከደቡብ ሱዳን የተነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው ጋምቤላ ክልል በመግባት በጎግ ወረዳ በሚገኘው ዲማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጽህፈት ቤቱ በፌስቡክ ገጹ እንዳለው በጥቃቱ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል እንዲሁም ሶስት ህፃናት ታፍነው ተወስደዋል።
የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት የጽህፈት ቤቱን ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግን ጠቅሶ እንደዘገበው ታጣቂዎች ከስደተኞች መጠለያ ጣቢያው በተጨማሪ በጎግ ወረዳ ከፑኝዶ ከተማ ወደ ቴዶ ቀበሌ ሲሄድ በነበረ ሞተር ሳይክል ላይ ባደረሱት ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት አልፏል።
የሙርሌ ታጣቂዎች ባለፈው ወር ወደ ጋምቤላ ክልል ዘልቀው በመግባት በንጹሃን ላይ ጥቃት ማድረሳቸውና የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡
የደቡብ ሱዳን መንግስት የሙርሌ ታጣቂዎች “በንጹሃን ላይ ባደረሱት ጥቃት ማዘኑን” በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ለአል-ዐይን ኒውስ መግለጻቸውም ይታወሳል።
“ጥቃቱ የመጀመርያ ባይሆንም የደረሰው ጉዳት ግን የሁሉም ጉዳት ነው” ነበርም ያሉት አምባሳደሩ ፡፡
በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ እና የጋምቤላ ንዌሮች መካከል በየጊዜው ታሪካዊ እና ባህላዊ ግጭቶን ማየት የተለመደ መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ የሚስተዋሉ ጥቃቶች “ከጀርባቸው ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎት” የሌላቸው እንደሆኑም አስረድቷል።
አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን አክለውም፤ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሁለቱም ሀገራት መንግስታት እንደተለመደው በትብብር እንደሚሰራም ገልጸው ነበር፡፡
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከዓመታት በፊት፤ በኑዌር ዞን እና አኙዋ ዞኖች ገብተው በርካታ ሕፃናትን አፍነው ሲወስዱ፣ ከአንድ መቶ ሰባ በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ማጣታቸውም እንዲሁ የሚታወቅ ነው።
ታጣቂዎቹ በወቅቱ ከ2 ሺህ በላይ ከብቶችን መዝረፋቸውን የተናገሩት ምክትል ሃላፊው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ደቡብ ሱዳን በመግባት ታፍነው ከተወሰዱት ሕፃናት መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑትን ከእገታ አስለቅቆ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሱም ይታወሳል።