ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል የገቡ የሙርሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የ8 ሰዎች ህይወት አለፈ
ታጣቂዎች ወደ ክልሉ ሰርጎ በመግባት ተደጋጋሚ ጥቃት በማድረስ ላይ መሆናቸውን የጋምቤላ ክልል አስታውቋል
በጥቃቱ አምስት ሰዎች መጎዳታቸውም ተገልጿል
ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል የገቡ የሙርሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የስምንት ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡
የጋምቤላ ክልል ሰላም ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኦቶው አኮት ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው በመግባት ጥቃት አድርሰዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ባደረሱት ጥቃት የስምንት ሠዎች ህይወት ሲያልፍ በአምስት ሠዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ባሳለፍነው ሳምንት በፈጸሙት ጥቃትም ሁለት ህጻናትን አግተው መውሰዳቸውን ኦቶው አኮት ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩት የሙርሌ ጎሳዎች ህጻናትን በማገት እና በመውሰድ እንደ ራሳቸው ልጆች አድርገው በማሳደግ ከብቶችን መጠበቅ እና ሌሎች ስራዎችን ማሰራት የተለመደ ባህል ነው፡፡
በጋምቤላ በዚህ ሰዓት በጋ ስለሆነ እና ክልሉን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚጎራብተው ድንበር ሰፊና ክፍት ስለሆነ የታጣቂዎች የመግባትና የመውጣት አዝማሚያ አለ ብለዋል።
“ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ፊቷን የምታዞርበት ምንም ምክንያት የለም”- አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን
“ዛሬም ወደፊትም ከደቡብ ሱዳን የሚመጣ ኢትዮጵያን ሊጎዳ የሚችል ነገር የለም”- ሪክ ማቻር
የሙርሌ ታጣቂዎች ትናንትና ድንበር አቋርጠው በመግባት በኑዌር ዞን አኮቦ ወረዳ በካንካን ቀበሌ ድንገተኛ ተኩስ በመክፈት የ8 ሠዎች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በ5 ሠዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል፡፡
ምክትል ሃላፊው አክለውም ክልሉ በአሁኑ ሰዓት ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻ በመጠቀም ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ስራውን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም አዋሳኝ የድንበር አካባው ሰፊ በመሆኑ ጥቃቱን ማስቆም አልተቻለም።
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከዓመታት በፊት፤ በኑዌር ዞን እና አኙዋ ዞኖች ገብተው በርካታ ሕፃናትን አፍነው ሲወስዱ፣ ከአንድ መቶ ሰባ በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።
ታጣቂዎቹ በወቅቱ ከ2 ሺህ በላይ ከብቶችን መዝረፋቸውን የተናገሩት ምክትል ሃላፊው የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ደቡብ ሱዳን በመግባት ታፍነው ከተወሰዱት ሕፃናት መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑትን ከእገታ አስለቅቆ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሱ ይታወሳል፡፡