መስክ ለመራጮች በየእለቱ 1 ሚሊየን ዶላር በእጣ መሸለሙ ክስ እንዲመሰረትበት አደረገ
ቢሊየነሩ የ2024ቱን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ይወስናሉ በተባሉ ሰባት ግዛቶች በእጣ የሚሰጠው ሽልማት መራጮች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል በሚል ነው የተከሰሰው
የቴስላ ባለቤቱ መስክ ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን 120 ሚሊየን ዶላር መስጠቱ ተገልጿል
አሜሪካዊው ቢሊየነር ኤለን መስክ ለመራጮች በየእለቱ በእጣ 1 ሚሊየን ዶላር መሸለሙ ክስ አስከትሎበታል።
የፊላደልፊያ ፍርድቤት መስክ የቀረበበትን ክስ እንዲያደምጥ በዛሬው እለት በችሎት እንዲገኝ አሳስቧል።
ክሱን ያቀረቡት አቃቤ ህግ ሌሪ ክራስነር የቴስላ፣ ስፔስኤክስ እና ኤክስ (ትዊተር) ባለቤቱ ኤለን መስክ ያቀረበው የ1 ሚሊየን ዶላር ሽልማት “ህገወጥ እና መራጮች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው” ብለዋል።
መስክ ከ12 ቀናት በፊት ነበር በሰባት የአሜሪካ ግዛቶች ለመምረጥ ለተመዘገቡና በኦንላይን ላቀረበው አቤቱታ የድጋፍ ፊርማቸውን የሚያኖሩ ሰዎች በእጣ ተለይተው 1 ሚሊየን ዶላር ሽልማት እንደሚሰጣቸው ያስታወቀው።
ሰባቱ ግዛቶችም አሪዞና፣ ጆርጂያ፣ ሚቺጋን፣ ኔቫዳ፣ ኖርዝ ካሮሊና፣ ፒንሲልቫኒያ እና ዊስኮንሲን ናቸው። እነዚህ ግዛቶች የአሜሪካን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት የሚወስኑ መሆናቸው ይነገርላቸዋል።
በእነዚህ ግዛቶች ለመራጭነት ተመዝግበው የመስክን የድጋፍ ፊርማ የፈረሙ መራጮች በየእለቱ 1 ሚሊየን ዶላር በሚያሸልመው እጣ እንዲሳተፉ ሲደረግ ቆይቷል።
የመጀመሪያው የ1 ሚሊየን ዶላር ሽልማት አሸናፊ ጆን ድርሄርም ጥቅምት 19 2024 በፒንሲልቫኒያ ሃሪስቡርግ ከመስክ ቼክ መቀበሉ የሚታወስ ነው።
የእጣ አወጣጡ ግልጽነት የጎደለ ነው ያሉት ክሱን የመሰረቱት ሌሪ ክራስነር፥ መስክ እና ለትራምፕ ድጋፍ የሚሰበስበው “ፒኤሲሲ” የተባለው ድርጅታቸው የ1 ሚሊየን ዶላር ሽልማቱን እንዲያቆሙ በፍርድ ቤት እንዲታገዱ ጠይቀዋል።
የመስክ እና የፒኤሲ ጠበቆች በቀረበው ክስ ዙሪያ እስካሁን ምላሽ እንዳልሰጡ ሬውተርስ ዘግቧል።
አንዳንድ የህግ ባለሙያዎች የመስክ የ1 ሚሊየን ዶላር ሽልማት ሰዎች ለመምረጥ እንዲመዘገቡና እንዲመርጡ ገንዘብ መክፈልን የሚከለክለውን የፌደራል ህግ ይጣረሳል ይላሉ።
በአንጻሩ መስክ በእጣው ውስጥ ይካተታሉ ያለው የድጋፍ ፊርማውን የሚያኖሩ ሰዎች ብቻ ናቸው ማለቱን የሚገልጹ የህግ ባለሙያዎች የሎተሪ ሽልማቱ ህገወጥ አይደለም በሚል ይከራከራሉ።
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር በበኩሉ የአሜሪካ “ፒኤሲ” የጀመረው የ1 ሚሊየን ዶላር ሽልማት የፌደራል ህጉን እንደሚጥስ ባለፈው ሳምንት መግለጹ ሲዘገብ ቆይቷል። ይሁን እንጂ የትኛውም የፌደራል አቃቤ ህግ እስካሁን በመስክ ላይ ክስ አልመሰረተም።
በፎርብስ የቢሊየነሮች ደረጃ በ195 ቢሊየን ዶላር ሃብት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኤለን መስክ ለሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ በይፋ ድጋፉን ገልጿል።
ቢሊየነሩ ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን 120 ሚሊየን ዶላር ከመለገስ ባለፈ ከትራምፕ ጋር በቅስቀሳ መድረኮች ላይ እየተገኘ ነው።
ዶናልድ ትራምፕም በድጋሚ ወደ ዋይትሃውስ ከዘለቁ ለዋነኛ ደጋፊያቸው መስክ ሹመት እንደሚሰጡት ቃል መግባታቸው ይታወሳል።