መስክ የድጋፍ ፊርማ ለሚፈርሙለት ሰዎች በየቀኑ 1 ሚሊየን ዶላር ለመሸለም ቃል ገባ
ቢሊየነሩ ለሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ 75 ሚሊየን ዶላር መለገሱ ተገልጿል
ኤለን መስክ የንግግር ነጻነትን የሚሰጠው የአሜሪካ ህገመንግስት እንዲከበር የሚጠይቅ የኦንላይን አቤቱታ ለጥፏል
አሜሪካዊው ቢሊየነር ኤለን መስክ በኦንላይን ለለቀቀው አቤቱታ የድጋፍ ፊርማቸውን ለሚያኖሩ ሰዎች በየቀኑ 1 ሚሊየን ዶላር ለመሸለም ቃል ገባ።
ሽልማቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እስከሚካሄድበት ህዳር 6 2024 ድረስ ይቀጥላልም ብሏል።
የኦንላይን አቤቱታው የንግግር ነጻነትን የሚፈቅደው የአሜሪካ ህገመንግስት እንዲከበር የሚጠይቅ ነው።
በፔንሲልቫኒያ የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በተሰበሰቡበት መድረክም ጆን ድርሄር የተባለ ግለሰብ የ1 ሚሊየን ዶላር ሽልማቱ አሸናፊ ሆኖ ከመስክ ቼክ እንደተሰጠው ሬውተርስ ዘግቧል።
የቴስላ፣ ኤክስ እና ስፔስኤክስ ባለቤቱ ኤለን መስክ በቀጣዩ ምርጫ ለሚወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ ድጋፉን ሰጥቶ በቅስቀሳው እያገዛቸው ነው።
“ፒኤሲ” ለተባለው ራሱ ላቋቋመው የምርጫ ቅስቀሳ ቡድንም 75 ሚሊየን ዶላር መስጠቱ ነው የተገለጸው።
የምርጫ ውጤትን ይወስናሉ በሚባሉ ግዛቶች መራጮች በነቂስ እንዲሳተፉ የሚቀሰቅሰው “ፒኤሲ” ከካማላ ሃሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ብርቱ ፉክክር ገጥሞታል ተብሏል።
ትራምፕ የግድያ ሙከራ በተደረገባቸው ፔንሲልቫኒያ በቅርብ ቀናት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ የተደረገው ግዙፍ የቅስቀሳ መድረክም ፉክክሩ መጠናከሩን እንደሚያሳይ ተዘግቧል።
የአወዛጋቢው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ደጋፊው ኤለን መስክ ቀጣዩን ምርጫ ሃሪስ ካሸነፈች የአሜሪካ የመጨረሻው ምርጫ ይሆናል፤ አሜሪካ አትኖርም ሲል ተናግሯል።
በትራምፕ ላይ ሁለት የግድያ ሙከራዎች መደረጋቸውን በማውሳትም ሃሪስ ላይ ይህ ለምን አልተደረገም በማለት ጠይቋል። መስክ ለራሱ ጥያቄ “አሻንጉሊትን መግደል እርባና ቢስ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ቢሊየነሩ የድጋፍ ፊርማ የጠየቀበት የኦንላይን አቤቱታ “የአሜሪካ ህገመንግስት አንደኛ እና ሁለተኛ ማሻሻያ የዜጎችን የንግግር ነጻነት እና ራሳቸውን ለመጠበቅ መሳሪያ የመታጠቅ መብት አስከብሯል፤ ከስር ፊርማየን በማኖር ህገመንግስቱ እንዲከበር የድጋፍ ቃሌን አረጋግጣለሁ” ይላል።
በትራምፕ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ የሚገኙ አካላት በአቤቱታው ላይ የድጋፍ ፊርማቸውን ያኖራሉ የተባለ ሲሆን፥ የ1 ሚሊየን ዶላር ሽልማቱ አሸናፊ በእጣ ይለያል።
የመስክ በየቀኑ የ1 ሚሊየን ዶላር ሽልማት ማዘጋጀት “ፒኤሲ” እንዲነቃቃ እና ትራምፕ የተሻለ መራጭ እንዲያገኙ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።