ኤለን መስክ ቢሊየን ዶላሮችን ከሚያስቀጣ ክስ በነጻ ተሰናበተ
መስክ በ2018 “ቴስላን የግል ንብረቴ ላደርገው ነው” በሚል ትዊተር ላይ የለጠፈው መልዕክት ለኪሳራ ዳርጎናል በሚል በባለአክሲዮኖች ተከሶ ነበር
የትዊተር መልዕክቱ የቴስላን ባለአክሲዮኖች ከ12 ቢሊየን ዶላር በላይ ማሳጣቱ ቢነገርም ፍርድ ቤት በነጻ አሰናብቶታል
የአሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች አምራቹ ቴስላ መስራች ኤለን መስክ፥ በቴስላ ባለአክሲዮኖች ከቀረበበት ክስ ነጻ ሆኗል።
የአለማችን ሁለተኛው ባለሃብት በ2018 ትዊተር ላይ ያጋራው መረጃ ነው ክስ ያስነሳበት።
መስክ በፈረንጆቹ ነሃሴ 7 2018 “ቴስላ የግል ንብረት ሊሆን ፈንድ ተገኝቷል፤ አንዱ አክሲዮንም 420 ዶላር ያወጣል” የሚል መረጃን ማጋራቱ ለቀናት የቴስላን የአክሲዮን ገበያ ከፍ አድርጎት እንደነበር ሬውተርስ አስታውሷል።
ባለሃብቱ ከሳኡዲ ቃልተገብቶልኛል ያሉት ገንዘብ ግን የውሃ ሽታ ሲሆን መረጃው ያልተጨበጠና የግል ስሜታቸውን ብቻ ያንጸባረቀ ነው በሚል ትችቶችን ማስተናገድ ጀመሩ።
የቴስላ የአክሲዮን ገበያውም ከከፍታ ወደ መንኮታኮቱ ሲመጣ ባለአክሲዮኖቹ ጉዳዩን በህግ ማየት ፈለጉ።
ባለአክሲዮኖቹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን ቀጥረው ሲያስጠኑም፥ “የመስክ መሰረተ ቢስ መረጃ” 12 ቢሊየን ዶላር ኪሳራን ይዞ መምጣቱ መረጋገጡን ነው ብሉምበርግ ያስታወሰው።
ጉዳዩንም በሳንፍራንሲስኮ የሚገኘው የአሜሪካ ፍርድ ቤት ለሶስት ሳምንታት ሲከታተለው ቆይቶ በትናንትናው እለት ኤለን መስክን ከተጠያቂነት ነጻ ያደረገ ውሳኔ ማሳለፉ ተነግሯል።
ፍርድ ቤቱ መስክን ጥፋተኛ ቢያደርግ ኖሮ ደረሰ ከተባለው የ12 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ባለፈ የቴስላ መስራቹ ባለሃብት ቀሪ አክሲዮኖቹን እንዲሸጥ እስከመገደድ ይደርስ ነበር ነው የተባለው።
ኤለን መስክ በ44 ቢሊየን ዶላር በገዛው ትዊተር ከክሱ በነጻ በመሰናበቱ ደስታውን አጋርቷል።
የቴስላ ባለአክሲዮኖች ጠበቃው ኒኮላስ ፖሪት ግን “የህግ የበላይነት በባለጠጎችም ላይ ሊታይ ይገባል” በማለት በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መከፋቱን ገልጿል።
የቴስላ፣ ስፔስ ኤክስ እና ትዊተር ባለቤቱ ኤለን መስክ በሚያጋራቸው አነጋጋሪ መልዕክቶች “ሚስተር ትዊተር” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል።
በቴስላ ባለአክሲዮኖች ቀርቦበት የነበረው ክስም የራሱን አመለካከት ሁሉ ትዊተር ላይ በስሜት ከመለጠፍ እንዲታቀብ ያስተምረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በፈረንጆቹ 2003 ቴስላን የመሰረተው ኤለን መስክ፥ በ2022 ብቻ ስምንት ጊዜ አክሲዮኖቹን ቢሸጥም የቴስላ ትልቁን ድርሻ እንደያዘ ነው።
13 ነጥብ 4 በመቶ የቴስላ ድርሻ (423 ነጥብ 6 ሚሊየን አክሲዮኖች) በመስክ ስም የተያዙ ናቸው።
ይህም በአክሲዮን ከተቋቋሙ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ትልቅ ባለድርሻ ያደርገዋል።