ሹመቱ ለትራምፕ እንዲመረጡ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ፈሰስ ያደረገው መስክን የበለጠ ተጽእኖ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ተብሏል
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቢሊየነሩ ኢለን መስክ አዲስ በሚቋቋመው ተቋም ሚና እንዲኖረው በትናንትናው እለት ሾመውታል።
ሹመቱ ለትራምፕ እንዲመረጡ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ፈሰስ ያደረገው መስክን የበለጠ ተጽእኖ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ተብሏል።
መስክ እና የቀድሞው የሪፐብሊካን ፕሬዝደንታዊ እጩ ቪቬክ ራማስዋሚ ትራምፕ የተጓተተውን የመንግስት አሰራርን በማሳጠር ቀልጣፋ አሰራር እንዲኖር ያስችላል ያሉትን አዲስ የተቋቋመውን 'ዲፓርትመንት ኦፍ ገቨርንመንት ኢፊሸንሲ' ወይም የውጤማነት ቢሮ ይመራሉ።
ትራምፕ ባወጡት መግለጫ መስክ እና ራሜስዋሚ "የእኔ አስተዳደር የመንግስት ቢሮክራሲ እንዲያፈርስ፣ ብዙ መመሪያዎችን እንዲቀንስ፣ ብክነትን እንዲቀንስ እና የፌደራል ኤጀንሲዎችን መዋቅር እንዲያስተካክል መንገድ ይጠርጋሉ" ብለዋል።
አዲሱ ዲፓርትመንት የሪፐብሊካን የረጅም ጊዜ ህልም እንደሆነ እና "ከመንግስት ውጭ ሆኖ ምክር እና መመሪያ እንደሚሰጥ" የገለጹት ትራምፕ የመስክ እና የራማስዋሚ ሹመት የሴኔት ይሁንታ የማያስፈልገው ይፋዊ ያልሆነ ሹመት መሆኑን አመላክተዋል። መስክም በትራምፕ ከተሰጠው ኃላፊነት በተጨማሪ የግዙፍ ማህበራዊ ሚዲያ ኤክስ፣ የቴስላ እና የስፔስ ኤክስ ኃላፊ ሆኖ እንዲቀጥል ያስችለዋል ተብሏል።
ፕራምፕ እንዳሉት አዲሱ ዲፓርትመንት "መጠነሰፊ የመዋቅር ለውጥ ለማፋጠን እና የቢዝነስ አስራርን ለመፍጠር" ከኃይትሀውስ እና ከበጀት ቢሮ ጋር ይሰራል።
ስራው የአሜሪካ ነጻነት በታወጀበት 250ኛ አመት መታበሲያ እለት ሐምሌ 2026 ይጠናቀቃል ተብሏል።
በፎርብስ መጽሄት የአለም ቁጥር አንድ ሀብታም ደረጃን የተቆናጠጠው መስክ ኩባንያዎቹ በትራምፕ ድል ምክንያት በተሻለ ሁኔታ እንዲታዩ ለማድረግ እየሰራ ነው።
መስክ ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከመስጠት ባለፈ በአደባባይ አብሯቸው በመታየት ድጋፉን ገልጿል።
መስክ በመንግስት ስራ መሳተፉ እንደ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ እና ክሪፕቶከረንሲ ያሉት ኩባንያዎቹ የገበያ ዋጋ እንዲጨምር ሊረዳው ይችላል።
ዶናልድ ትራምፕ የዲሞክራቷን እጩ ካማላ ሀሪስን በማሸነፍ በድጋሚ ወደ ኃይት ሀውስ መግባት ችላዋል። ትራምፕ ለኃይት ሀውስ ኃላፊነት ጨምሮ ለበርካታ የመንግስት የስልጣን ቦታዎች አጋሮቻቸውን እየሾሙ እና እያጩ ይገኛሉ።