የኤለን መስኩ ኤክስ ለሰራተኞቹ ቃል የገባውን ጉርሻ ባለመክፈሉ ፍርድቤት ሊቀርብ ነው
የሳንፍራንሲስኮ ፍርድ ቤት ኤክስ በሰራተኞቹ የቀረበበት አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግለት ያቀረበውን ጥያቄ አልተቀበለውም
የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊየን ዶላር መግዛታቸው ይታወሳል
የኤለን መስኩ ኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ለሰራተኞቹ ቃል የገባውን አመታዊ ጉርሻ ወይም ቦነስ ባለመክፈሉ ፍርድቤት ቆሞ ሊከራከር ነው ተባለ።
መስክ በሚያዚያ ወር 2022 ትዊተርን በ44 ቢሊየን ዶላር ከገዙ በኋላ የካሳ ክፍያ እና አመታዊ ጉርሻ ወይም ቦነስ ጉዳይ ሰራተኞቹን ስጋት ውስጥ መጣሉ ይታወሳል።
ቢሊየነሩ ግዙፉን የማህበራዊ ትስስር ገጽ በእጃቸው ማስገባታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የጉርሻ ክፍያው እንደማይቀር ሲናገሩ እንደነበር ሰራተኞቻቸው ያወሳሉ።
በስራቸው ያሉ ስራ አስፈጻሚዎችም የ2022 ጉርሻ ወይም ቦነስ ክፍያ እንደሚፈጸም ለሰራተኞቹ ሲገልጹ መቆየታቸውን ነው በሳንፍራንሲስኮ የፌደራል ፍርድቤት የቀረበው አቤቱታ የሚያሳየው።
በኩባንያው የካሳ ክፍያ ከፍተኛ ዳይሬክተር የነበረውና በግንቦት ወር 2023 ስራውን የለቀቀው ማርክ ስኮቢንገር ቅሬታ ያቀረቡትን የኤክስ ሰራተኞች ወክሎ ያቀረበው አቤቱታ ኩባንያው የጉርሻ ክፍያውን እንዲፈጽም ይጠይቃል።
አሁን በስራ ያሉትን ጨምሮ በመስክ ወጪ የመቀነስ የሪፎርም እርምጃ የተሰናበቱ የቀድሞ ሰራተኞችም ክፍያውን ማግኘት አለባቸውም ይላል።
የሳንፍራንሲስኮ የፌደራል ፍርድቤትም ስኮቢንገር ያቀረበው አቤቱታ አሳማኝና ለክርክር ስለሚያበቃ ክስ መመስረት ይቻላል የሚል ውሳኔ አሳልፏል።
ኤክስ ግን ሰራተኞቹ ቃል ተገባላቸው እንጂ በውል የሰፈረ ነገር ስለሌለ ተጠያቂ ልሆን አይገባም ብሏል።
“ትዊተር (ኤክስ) ለሰራተኞቹ የማይፈጽማቸውን ቃልኪዳን ይገባል፤ መከፈል የነበረበትን ጉርሻ ባለመክፈሉ ስራዬን ለቅቄያለሁ ያለው የቀድሞው የኩባንያው ባልደረባና የካሳ ዳይሬክተር ማርክ ስኮቢንገር የቀድሞ ባልደረቦቹን ወክሎ የሚያቀርበው ክስ ይጠበቃል።
የቴክኖሎጂ ኩባንያው ጠበቆችም ፍርድ ቤት እየተመላለሱ ለመከራከር ይገደዳሉ ተብሏል።
ኤለን መስክ ትዊተርን እንደገዙ ፈጥነው እርምጃ የወሰዱት ሰራተኞችን መቀነስ እንደነበር ይታወሳል።
ቢሊየነሩ ከ6 ሺህ በላይ ሰራተኞችን አሰናብተው የኩባንያውን ሰራተኞች ቁጥር ወደ 1 ሺህ 500 እንዳወረዱት ለቢቢሲ በሰጡት ቃለመጠይቅ መናገራቸውም አይዘነጋም።