ቢል ጌትስ፣ ኤለን መስክ እና ማርክ ዙከርበርግ በጋራ ጉዳይ እየመከሩ ነው
አሜሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ የዓለማችን የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለቤቶችን ለስብሰባ ጠርታለች
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን መቆጣጠር የሚያስችል ፖሊሲ ማዘጋጀት አስፈልጓል ተብሏል
የዓለም ቴኖሎጂዎችን በመምራት የሚታወቁት አሜሪካዊያን ባለጸጋዎች ለብርቱ ጉዳይ በዋሸንግተን ተገናኝተዋል።
የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ ባለቤት ቢል ጌትስ፣ የቴስላ፣ ስታርሊንክ እና ኤክስ ወይም በቀድሞ ስሙ ትዊተር ኩባንያ ባለቤቱ ኤለን መስክ እንዲሁም የሜታ ኩባንያ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ ከሌሎች ባለጸጋዎች ጋር በጋራ እየመከሩ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የጎግል፣ ኦፕን አይ እና ሌሎች የዓለማችን የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለቤቶች እና መሪዎች ጋር እየተደረገ ያለው ይህ ስብሰባ በአሜሪካ መንግስት የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
የነዚህ ባለጸጋዎች የስብሰባ አጀንዳ ደግሞ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ሲሆን ዋሸንግተን በዚህ ዙሪያ የቁጥጥር ፖሊሲ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነች ተገልጿል፡፡
የፌስቡክ መስራችና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ በአንድ ቀን 29 ቢሊየን ዶላር ማጣቱ ተገለፀ
ይህ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ከመጽደቁ በፊት ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር ውይይት በማስፈለጉ ስብሰባው ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡
በቴክኖሎጂው መስክ የተሰማሩት ኩባያዎች የቁጥጥር ፖሊሲ እንዲዘጋጅ ሲወተዉቱ መቆየታቸውን ዘገባው አክሏል።
የሰው ልጆችን ህይወት ከመቼውም ጊዜ በላይ አቅልሏል የሚባለው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ መልሶ የሰው ልጆችን ህይወት እያወሳሰበ ነው በሚል ይተቻል፡፡
ቴክኖሎጂው በተለይም ከዚህ በፊት በሰው ልጆች ይሰሩ የነበሩ ስራዎችን እየነጠቀ ነው፤ የሰው ልጅ የአዕምሮ ስራዎችን ያለ ክፍያ ሌሎች እንዲጠቀሟቸው ያደርጋል የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ወቀሳዎች ይቀርብበታል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ገዳይ ቫይረስ ሊሰራጭ ይችላል የሚሉ ባለሙያዎች፥ ቴክኖሎጂው አውዳሚ ክስተቶችንም ሊፈጥር እንደሚችል ስጋታቸውን እያጋሩ ነው።