ከተመልካቾች የሚገኘው ገቢም ለሆስፒታል ግንባታ እንደሚውል ተገልጿል
የሁለቱ ቢሊየነሮች የኢለን መስክ እና ማርክ ዙከርበርግ ፍልሚያ በሮም እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኢለን መስክ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ ነበር ለተፎካካሪው የሜታ ኩባንያ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ የእንፋለም ጥያቄ ያቀረበው፡፡
ዙከርበርግም የኢለን መስክ ጥያቄ መቀበሉን ከተናገረ በኋላ ሁለቱም አካላት በየግላቸው ልምምድ በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ አሜሪካዊያን ፍልሚያ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን ፍልሚያው የሚካሄድበት ቀን እና ቦታም ይፋ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡
አሁን ላይ ይህ ጥያቄ በከፊል የተመለሰ ሲሆን ውድድሩ በጣልያን መዲና ሮም እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
ኢለን መስክ ስለ ውድድሩ ሁኔታ ከጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂዮ ሜሎኒ እና ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ጋር መወያየቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሁለቱ ባለጸጋዎች ፍልሚያ የቀድሞ የሮም ፍልሚያ ባህልን በጠበቀ መልኩ ይካሄዳል የጠባለ ሲሆን ውድድሩ ለተመልካቾች ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ከውድድሩ መግቢያ ቲኬት የሚገኘው ገቢም ለበጎ አድራጎት ስራዎች ይውላል የተባለ ሲሆን በተለይም የህጻናት ሆስፒታል ግንባታ ይውላልም ተብሏል፡፡
እንዲሁም የዓለማችን ባለጸጋዎች በበጎ ፈቃደኝነት ተጨማሪ ገንዘብ የሚለግሱበትን መንገድ በመፍጠር ተጨማሪ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡
ኢለን መስክ እና ማርክ ዙከርበርግ በቴክኖሎጂ ፉክክር ውስጥ ያሉ ስራ ፈጣሪዎች ሲሆኑ ሜታ ኩባንያ ከሁለት ወር በፊት ይፋ ባደረገው ትሪድስ የተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ክስ ቀርቦበታል፡፡
ኢለን መስክ በሜታ ለይ ክስ የመሰረተው በቀድሞ ስሙ ትዊተር ኩባንያ ከስራ የተሰናበቱ ሰራተኞችን በመቅጠር የድርጅቴን ሚስጢሮች ወስዶብኛል በሚል ነው፡፡