ከሚለቀቁት ሰዎች መካከል የብሪታንያ የቀድሞ አምባሳደር ቪኪ ቦውማንን ጨምሮ የአውስትራሊያ እና ጃፓን ዜጎች ይገኙበታል
የማይናማር ጁንታ 6 ሺህ የሚጠጉ እስረኞችን ሊለቅ ነው። ወታደራዊው መንግስት የሀገሪቱን ብሄራዊ የድል ቀን በማስመልከት ነው እስረኞቹን የሚፈታው።
ከሚለቀቁት ሰዎች መካከል የብሪታንያ የቀድሞ አምባሳደር ቪኪ ቦውማ ይገኙበታል።
አውስትራሊያዊው የቀድሞዋ የማይናማር መሪ ኡንግ ሳን ሱኪ አማካሪው ሲን ቱርኔልና የጃፓን ዜግነት ያለው ጋዜጠኛም ከእስር እንደሚፈቱ ተገልጿል።
የማይናማር ጁንታ የተለቀቁት የውጭ ሀገራት እስረኞች መጠንን ግን አልገለፀም።
በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን ኡንግ ሳን ሱኪን በየካቲት ወር 2021 በሃይል ያነሳው ጁንታ፥ በመላ ሀገሪቱ ተቃውሞው በርትቶበታል።
ለተቃውሞ አደባባይ የወጡትን በማሰርም ውጥረቱን ለማርገብ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
እስካሁንም ከ16 ሺህ በላይ ሰዎችን ማሰሩን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
ወታደራዊ ሀይሉ በሀይል ስልጣን ከያዘ ወዲህ ከ2 ሺ 400 በላይ ሰዎች መገደላቸውንም የፖለቲከኛ እስረኞችን ለመደገፍ የተቋቋመ ማህበር ገልጿል።
ወታደራዊ ሃይሉ 6 ሺ የሚጠጉ እስረኞችን መልቀቁ አለም አቀፉን ጫና ለመቀነስ ያለመ ስለመሆኑ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ያለምንሞ ጥፋት እና ህጋዊ ክስ በእስር ላይ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የማይናማር እና የሌሎች ሀገራት ዜጎች እንዲፈቱ ጠይቋል።