ተመድ ፡“የምያንማር ወንጀል ፈጻሚዎች ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ማወቅ አለባቸው” ሲል አስጠነቀቀ
የምያንማር ወንጀል ጉዳዮች የሚያጣራው ቡድን “አጥፊዎች እንዲጠየቁ ማስረጃዎቹን እየሰበሰብኩ ነው” ብሏል
የምያንማር ጁንታ በቅርቡ በአራት የዴሞክራሲ ተሟጋቾችን ላይ የወሰደውን የግዲያ እርምጃ ዓለምን ማስቆጣቱ አይዘነጋም
ባለፈው አመት ከተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በኋላ በምያንማር እየተፈጸተሙ ያሉ ወንጀሎች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱ ተባበሩት መንግስታት መረጃዎች ያስረዳሉ።
በምያንማር ጉዳይ የመብት ጥሰቶችን እና በጣም ከባድ የሆኑትን ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን የሚያጣራውና እንደፈረንጆቹ በ2018 የተዋቀረው የተመድ መርማሪ ቡድን፤ በሀገሪቱ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች ለመኖራቸው የሚያመላክቱ ማስረጃዎች ማግኘቱን ባወጣው ሪፖርት አመላክቷል።
መርማሪ ቡድኑ ባወጣው ሪፖርት "ከየካቲት 2021 ጀምሮ በማላው ምያንማር በሰው ልጆች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያመለክቱ ቪዲዮዎችን፣ ፎቶግራፎችን እና ሰነዶችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የመረጃ እቃዎችን መሰብሰብ ችለናል" ብሏል።
የተመድ መርማሪ ቡድን ኃላፊ ኒኮላስ ኩምጂያን በሰጡት መግለጫ "የእነዚህን ወንጀሎች ፈጻሚዎች ያለቅጣት እርምጃ መቀጠል እንደማይችሉ ማወቅ አለባቸው" ሲሉ አሳስበዋል።
አክለውም፡ አንድ ቀን በህግ እንዲጠየቁ ማስረጃዎቹን እየሰበሰብን እያቆየን ነው ብለዋል ኃላፊው።
በከፍተኛ የሰብዓዊ ጥሰት ድርጊቶች የሚከሰሰው የምያንማር ወታደራዊ ጁንታ በቅርቡ በአራት የዴሞክራሲ ተሟጋቾችን ላይ የወሰደውን የግዲያ እርምጃ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ያስቆጣ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ድርጊቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባቼሌት በሰጡት መግለጫ ፤ ወታደራዊ አገዛዙ በአራቱም ሰዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ፤በህዝቡ ላይ እያካሄደ ያለውን የጭቆና ዘመቻ ማራዘሚያ እንደሆነ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
በወቅቱ "በጣም አዝኛለሁ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጭካኔያቸው ሊቀጣቸው ይገባል" ያሉት ደግሞ የምያንማር ብሔራዊ አንድነት መንግስት ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ክያው ዛው ናቸው።
በቀጠናው የመብት ተሟጋች ተቋም የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ኤርዊን ቫን ዴር ቦርግት በበኩላቸው “እነዚህ ግድያዎች በዘፈቀደ የሰዎችን ህይወት ማሳጣት ሌላው በምያንማር ያለው አስከፊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ማሳያዎች ናቸው” ብለዋል።