ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ኩባንያዎች ገንዘብ እንዲመዘብሩ ያሰመራቻቸው ዜጎች
ፒዮንግያንግ በሀሰተኛ መታወቂያ እና ማንነት የምታስቀጥራቸው ዜጎች 88 ሚሊየን ዶላር መመዝበራቸው ተሰምቷል

“አይቲ ዋርየርስ” በመባል ከሚታወቁት ከእነዚህ ሰዎች መካከል አሜሪካ በ14ቱ ላይ ክስ ከፍታለች
ሰሜን ኮሪያውያን በበይነ መረብ በሚሰሩ ስራዎች ላይ በሀሰተኛ ስም እና መታወቂያ በመመዝገብ ከተለያዩ የአሜሪካ ኩባንያዎች ገንዘብ ሲዘርፉ እንደነበር ተሰምቷል፡፡
ግለሰቦቹ ከተቀጠሩባቸው ተቋማት በተለያዩ መንገዶች የሚዘርፉትን ገንዘብ ለፒዮንግያንግ የጦር መሳሪያ ግንባታ ይልኩ እንደነበር ነው የተነገረው፡፡
ባለፉት 6 አመታትም በዚሁ የወንጀል እንቅስቃሴ የተሰማሩ በሺዎች ከሚቆጠሩ ግለሰቦች 88 ሚሊየን ዶላር ወደ ሰሜን ኮሪያ መላኩ ተገልጿል፡፡
በሴንትሉዊስ የሚገኝ የፌደራል ፍርድ ቤት ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 14 ሰሜን ኮሪያውያንን ክስ መመልከት ጀምሯል፡፡
ግለሰቦቹ በኦንላይን ማጭበርበር፣ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ህገወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ፣ በማንነት ስርቆት እና ሌሎችም ክሶች ቀርቦባቸዋል፡፡
አቃቤ ህግ ተጠርጣሪዎቹ መቀመጫቸውን በሩስያ እና ቻይና ላደረገ “ሲልቨርስታር” ለተባለ የሰሜን ኮርያ ድርጅት ሲሰሩ እንደቆዩ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
እንደ አሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ ግለሰቦቹ “አይቲ ዋርየርስ” በሚል ስም የሚታወቁ ሲሆን ባለፉት ስድስት አመታት ከአውሮፓ እና አሜሪካውያን ዜጎች የሰረቋቸውን መታወቂያዎች አመሳስለው በመስራት በሀሰተኛ ማንነት ቅጥር ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡
ማንንትን ከመስረቅ በተጨማሪ በአሜሪካ ለሚኖሩ አሜሪካውያን ገንዘብ በመክፈል በላፕቶፖች ላይ በሚጫን ሶፍትዌር ስራ የሚሰሩት በዛው በአሜሪካ እንደሆነ ለማስመሰል ይጥሩ ነበር ተብሏል፡፡
በአሜሪካውያን ኩባንያዎች ውስጥ በወር እስከ 10 ሺህ ዶላር ድረስ ደመወዝ ክፍያ የሚቀጠሩት የኮምፕዩተር ባለሙያዎች በድርጅቶቹ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ የተለያዩ ሚስጥራዊ ሰነዶችን በመስረቅ በማስፈራራት የሚሰበስቡትን ገንዘብ ለሰሜን ኮርያ ጦር መሳርያ ማበልጸጊያ ፕሮግራሞች ሲለግሱ መቆየታቸውን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከዚህ ስራ ጋር በተገናኘ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን ማንነት በተመለከተ ጥቆማ ለሚሰጥ ማንኛውም አካል የአምስት ሚሊየን ዶላር ሽልማት ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡