ደቡብ ኮሪያ እና የአውሮፓ ህብረት የሰሜን ኮርያ ወታደሮች ከሩስያ ለቀው እንዲወጡ አሳሰቡ
ሀገራቱ የሶስተኛ ሀገር ወታደር በጦርነቱ በቀጥታ መሳተፍ ግጭቱን የሚያባብስ እና የሌሎች ሀገራትን ተሳትፎ የሚጠራ ነው ብለዋል
ህብረቱ ከደቡብ ኮሪያ ጋር በአይነቱ የመጀመሪያ የተባለውን ስትራቴጂካዊ ውይይት አድርጓል
ደቡብ ኮሪያ እና የአውሮፓ ህብረት ሰሜን ኮርያ ለሩሲያ የላከችውን ጦር በፍጥነት እንድታስወጣ ጠየቁ፡፡
ሁሉቱ አካላት ለመጀመርያ ጊዜ ባደረጉት ስትራቴጂካዊ ውይይት ፒዮንግያንግ ለሞስኮ ታደርገዋለች ያሉትን የጦር መሳርያ ድጋፍ አውግዘው የሶስተኛ ሀገር በጦርነቱ ያለውን ተሳትፎ አደገኛነት አመላክተዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሀላፊ ጆሴፍ ቦሬል በትላንትናው እለት ወደ ሴዑል አቅንተው ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቾቴ ዩል ጋር መክረዋል፡፡
በተጨማሪም የሳይበር ደህንነት እና ትጥቅ ማስፈታትን ጨምሮ 15 ዘርፎችን የሚሸፍን የደህንነት እና የመከላከያ አጋርነት ተፈራርመዋል።
ውይይቱን ተከትሎ ባወጡት የጋራ መግለጫ ከ8-10 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ኮርያ ወታደሮች በሩሲያ ኩርሰክ ክልል መሰመራታቸው መረጋገጡን ነው የገለጹት፡፡
ቦሬል በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ ላይ በለጠፉት ጽሁፍ “ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርሰው ጥቃት የህልውና ስጋት ነው፤ ደቡብ ኮርያ ይህን ስጋት በሚገባ ትገነዘባለች ለዩክሬን በሚደረገው ድጋፍም በጋራ እንቆማለን” ብለዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቾ በፒዮንግያግ እና በሞስኮ መካከል እየተጠናከረ የመጣውን አጋርነት ተከትሎ ሴዑል ለዩክሬን የጦር መሳርያ ድጋፍ ታደርግ እንደሆን ተጠይቀው ጉዳዩ እየተመከረበት ይገኛል ሲሉ መልሰዋል፡፡
እስካሁን ባለው ለዩክሬን የጦር መሳርያ ድጋፍ እንድታደርግ የቀረበላትን ድጋፍ ውድቅ ያደረገችው ደቡብ ኮርያ የሰብአዊ እርዳታ እና መሬት ውስጥ የሚቀበሩ ፈንጆችን ማውጣት የሚችል መሳርያ ለዩክሬን ለግሳለች፡፡
ጦሯን ወደ ሩሲያ የላከችው ሰሜን ኮርያ ፤የስለላ ሳተላይት ለማምጠቅ እና የሚሳኤል አቅሟን ለማሳድግ የሚያግዙ ወታደራዊ እና የሲቪል ቴክኖሎጂዎች ድጋፍ ከሩሲያ ሊደረግላት እንደሚችል የሴዑል የደህንነት ተቋማት አስጠንቅቀዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንትም “ሁዋሶንግ -19” የተባለ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ በማድረግ ወታደራዊ አቅሟን ለማሳየት ሙከራ አድርጋለች፡፡
ከሰሞኑ በሩስያ እንደሚገኙ የተረጋገጠው የሰሜን ኮሪያ ጦር አባላት በቅርቡ ከሩሲያ ድንበር ተሻግረው በዩክሬን ግዛት ውስጥ ሊሰማሩ እንደሚችሉ አሜሪካ ይፋ አድርጋለች፡፡
ፒዮንግያነግ በበኩሏ በሞስኮ ጉብኝት ላይ በሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ በኩል ሩሲያ የዩክሬን ጦርነትን እስክታሸንፍ ድረስ ድጋፏ እንደማይቋረጥ አስታውቃለች፡፡