በኮፕ28 የሚደረሱ ስምምነቶች አለማችን ከተጋረጠባት ፈተና ይታደጋሉ - ነቢል ሙኒር
በኮፕ27 የ78 ሀገራት የተደራዳሪ ቡድን መሪ የነበሩት አምባሳደር ነቢል ሙኒር ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ አድርገዋል
አምባሳደሩ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና የሚፈታው በመደማመጥና በመተባበር ብቻ ነው ብለዋል
ፓኪስታን ለአለም የከባቢ አየር ብክለት ያላት ድርሻ ከ1 በመቶ ብቻ ነው።
ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትመደባለች።
በጀርመን ዋች በሚወጣው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ደረጃ ኢስላማባድ በተከታታይ አመታት እስከ 10ኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ናት።
በደቡብ ኮሪያ የፓኪስታን አምባሳደርና በኮፕ27 የ78 ሀገራት የተደራዳሪዎች ቡድን መሪው ነቢል ሙኒር ሀገራቸውም ሆነች አለማችን ስለተጋረጠባት የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አምባሳደር ነቢል ሙኒር በዱባይ የሚካሄደው ኮፕ28 በ2015 በፓሪስ የተደረሱ ስምምነቶች አፈጻጸም በጥልቀት የሚገመገምበት እና ከተሳሳተ አካሄዳችን የምንመለስበት አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነው ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ የባለሙያዎች ቡድን ሪፖርት በግልጽ መስመር መሳታችን አሳይቷል የሚሉት አምባሳደር ሙኒር፥ በኮፕ28 ጉባኤ የአለማችን መጻኢ የሚወስኑ ስምምነቶች ይጠበቃሉ ባይ ናቸው።
“በዱባዩ ጉባኤ ሀገራት እርስ በርስ መደማመጥና መግባባት ይኖርባቸዋል፤ በወንድማማችነት መንፈስ ለጋራ መፍትሄ ሊሰሩ ይገባል” ነው ያሉት።
የአየር ንብረት ለውጥን መቀነስ የሚቻለው በትብብር ብቻ መሆኑን በመጥቀስም ሀገራት ከራሳቸው ፍላጎት ውጭ የሌሎችን ስጋትና ፍላጎት ማድመጥና ምላሽ መስጠት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የኮፕ28 ጉባኤ ካለፉት ጉባኤዎች በተሻለ ሀገራት ለአለማችን መጻኢ መለወጥ ቁርጠኝነታቸውን የሚያሳዩበት እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።