ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጥምር መንግስት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ፈቃድ አገኙ
ኔታንያሁ ጥምር መንግስት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ዕድል ሲያገኙ የአሁኑ ለ5ኛ ጊዜ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ28 ቀናት ውስጥ ጥምር መንግስት እንዲመሰርቱ በፕሬዝዳንቱ ታዘዋል
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጥምር መንግስት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ከፕሬዝዳንት ሩቨን ሪቭሊን አገኙ፡፡
ፕሬዝዳንት ሪቭሊን ፍቃዱን የሰጡት የሃገሪቱ ምክር ቤት (ክኔሴት) የሊኩድ ፓርቲ አባላት ኔታንያሁን በመደገፋቸው ነው፡፡
በዚህም ኔታንያ በቀጣዮቹ 28 ቀናት ውስጥ መንግስት ሊመሰርቱ የሚችሉበትን ዕድል በደብዳቤ ፈርመው ሰጥተዋል፡፡
ሪቭሊን ለኔታንያሁ እንዲህ ዓይነት ፈቃድ ሲሰጡ የአሁኑ ለ5ኛ ጊዜ ነው፡፡
ይህ ይሆናል የሚል ግምት እንዳልነበራቸው ነው ከ7 ዓመታት በፊት በፕሬዝዳንትነት የተሾሙት አዛውንቱ የሚናገሩት፡፡
የምክር ቤቱን እምነት አግኝቶ መንግስት ሊመሰርት የሚችለው አካል የትኛው ይሆን የሚል ሃሳብ እንደነበራቸውም ገልጸዋል፡፡
ሆኖም በዚህኛውም ምርጫ በተናጠል መንግስት ሊያስመሰርተው የሚችል ድምጽ ያገኘ ፓርቲ አልተገኘም፡፡
“የትኞቹም እጩዎች ጥምረት ሊፈጥሩ የሚችሉበት እድል የላቸውም” በሚል አስተሳሰብ ውስጥ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት፡፡
“በህግ የተጠያቂነት ሂደት ላይ የሚገኝን አካል መንግስት እንዲመሰርት እድል መስጠቱ ይከብዳል”ም ነው ሪቭሊን ያሉት፡፡
ሆኖም “የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመፍቀዱ ምክንያት ራሳቸውን ከጉዳዩ ለማግለል መወሰናቸውን”ም አዛውንቱ ተናግረዋል፡፡
በህግ የተጠያቂነት ሂደት ውስጥ ያለን አካል “የመከልከሉ ስልጣን የምክር ቤቱ” እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም እና ከሙስና ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጉዳዮች ተከሰው በፍርድ ሂደት ላይ በሚገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጉዳይ ትናንት የምስክሮች ቃል መሰማቱ የሚታወስ ነው፡፡
ዛሬ ቃለ መሃላ በፈጸመው በአዲሱ የእስራኤል ምክር ቤት የ13 ፓርቲ ተወካዮች ይገኛሉ፡፡
ተወካዮቹ ጥምር መንግስት የመመስረቱን ሂደት በተመለከተ ከፕሬዝዳንቱ ጋር የመከሩ ሲሆን የ4 ፓርቲ ተወካይ የሆኑ 52 የምክር ቤቱ አባላት የኔታንያሁን ለተግባሩ መታጨት ደግፈዋል፡፡
ሌሎች የ4 ፓርቲ ተወካይ የሆኑ 45 የምክር ቤቱ አባላት ደግሞ የየሽ አቲድ ፓርቲ መሪው ዬር ላፒድ መንግስት እንዲመሰርቱ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡
ያሚና ፓርቲ የራሱን መሪ ንፍታሌም ቤኔትን በእጩነት አቅርቧል፡፡
ሌሎች ሶስት ፓርቲዎች ደግሞ ማንንም በአጩነት አላቀረቡም አልደገፉምም፡፡
እስራኤል በሁለት ዓመታት ውስጥ ለ4ኛ ጊዜ ምርጫ ማካሄዷ የሚታወስ ነው፡፡