በ”ሕግ ማስከበር ሽፋን” ሕፃናትን ጨምሮ 35 ዜጎች ያለፍ/ቤት በፀጥታ ሃይሎች መገደላቸውንም ገልጸዋል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ መንግስት ሕግ የማስከበር ስራ ባለው ዘመቻ 40 አባሎቹና አመራሮቹ እንደታሰሩበት አስታወቀ፡፡
የንቅናቄው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊና የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል ክርስቲያን ታደለ ሕግ ለማስከበር በሚል “ሕግ እየተጣሰ ሕፃናትን ጨምሮ 35 የሚደርሱ ዜጎች ያለፍርድ በፀጥታ አካላት ተገድለዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ክርስቲያን ይህንን ያሉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው፡፡
በም/ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ክርስቲያን 40 የሚጠጉ የድርጅታቸው መዋቅር አመራሮችና አባላት መታሰራቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን "አስሮ መመርመር በሀገሪቱ ሕግ የተፈቀደ" እንዳልሆነ ያነሱት አቶ ክርስቲያን አሁን ላይ ከድርጅታቸው አባላት ባለፈም ከ 20 በላይ ጋዜጠኞች መታሰራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለፍርድቤት ትዕዛዝ በቀንና በሌሊት በፀጥታ አካላት እየታፈኑ ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውንና ወሰወራቸውን ያነሱት የአብን ተወካይና የም/ቤቱ አባል፤ እስካሁንም ፍርድቤት ያልቀረቡና ቤተሰብ ያልጠየቃቸውና የት እንዳሉ የማይታወቁ ዜጎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
መንግስት “በመረጠኝ ሕዝብ ላይ በተለያዩ አካላት የመግለጫና ፕሮፖጋንዳ ድጋፍ ጭምር የተቀናጀ ዘመቻ በመክፈት ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዳይከውን እያጉላላው ይገኛል” ሲሉም ነው የፓርላማ አባሉ የጠየቁት።
የአብን የፓርላማ አባላት በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ነው ያሉት "መንግስታዊ እገታና ስወራ" በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቁ
ሕግ መከበር እንዳለበት እንደሚያምኑ ያነሱት አቶ ክርስቲያን "ሕግ በመጣስ እና ሕዝብን በማሸብር ግን ሊሳካ አይችልም" ሲሉም ተናግረዋል በስብሰባው፡፡
በሕግ ማስከበር ሽፋን የመንግስት ተቺዎችንና የተቃውሞ ድምፆችን በማፈን፣ ስጋትና ፍርሃት የሰፈነበት የሙያ ምህዳር በመሻት መንግስት የዴሞክራሲ ግንባታን እንዴት እውን ሊያደርግ እንደሚችል አቶ ክርስቲያን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡
የታፈኑና ከፍርድ ውጭ በኮንሰንትሬሽን ካምፕ ያሉ ዜጎችና አባሎቻችን አስቸኳይ ፍትሕ እንዲሰጣቸውም አቶ ክርስቲያን ጠይቀዋል፡፡