ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዩናይትድ አረብ ኢምሬቶች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከተውጣጡ ኢትዮጵያውያንና ጋር ተወያይተዋል
በዩናይትድ አረብ ኢምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የማምለኪያ ቦታ ተሰጥቷቸውል፤ የታሰሩትም ተፈተዋል
በዩናይትድ አረብ ኢምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የማምለኪያ ቦታ ተሰጥቷቸዋል፤ የታሰሩትም ተፈትተዋል
በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በተለያየ የስራ መስክ ተሰማርተው እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ ከሀገር የወጡበት ምክንያት ቢለያይም በእነዚህ ሀገራት የሚደርሱባቸው ችግሮች፣ የሚያጋጥሟቸው ውጣውረዶች ተመሳሳይ መሆናቸው ይነሳል፡፡
ወደ መካከለኛው ምስራቅ ከሚሄዱ ዜጎች መካከል በርካቹ ሴቶች ሲሆኑ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ ናቸው፡፡ ይሁንና በእነዚህ ሀገራት ኢትዮጵያውያን ላይ በርካታ ግፎች ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡በዐይን ከሚታዩት ግፎች በተጨማሪም በእስር ቤቶች ውስጥ የነበሩ ዜጎች በደል ይደርስባቸው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ ዜጎችን ትኩረት ያደረገ የዲፕሎማሲ ስራ መጀመራው ይታወሳል፡፡በዚህም መሰረት በእስር የነበሩ፣የመኖሪያ ፈቃድ ያልነበራቸውና በጥቅሉ ችግር ላይ የነበሩ ዜጎች ከስቃይና ከተስፋ መቁረጥ እንዲወጡ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በግብጽ፣ታንዛኒያ፣ኬንያና ሌሎች ሃገራት ችግር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲፕሎማሲ ጥረት ከእስር መፈታታቸው ብሎም ወደ ሃገር ቤት መግባታቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም በአዲሱ የውጭ ጉዳይና ሃገራዊ ደህንነት ፖሊሲ ውስጥ ትልቅ ጉዳይ ተደርጎ ተነስቷል፡፡
ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመካከለኛው ምስራቅ የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በቆይታቸውም በአቡዳቢና በዱባይ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአቡዳቢ ቆይታ
ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከተወጣጡ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተወካዮች ተወያይተው ነበር፡፡
ከ250 በላይ ከሚሆኑ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የተወጣጡ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተወካዮችም በሃገራቱ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተመለከተ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በየሚኖሩባቸው ሀገራት የአምልኮ ስፍራዎች እና ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ቦታዎችን ማግኘት በሚችሉባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከላይ በተጠቀሱት እና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች እና ተግዳሮቶች ዙሪያ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በኢትዮጵያውያኑ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዱባይ ቆይታ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዜጎች መከበር የሃገር መከበር መሆኑን በመገንዘብ መንግስት የዜጎችን መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ከተለያዩ የዓረብ ሀገራት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያንን በዱባይ አል አህሊ ስታዲየም ባወያዩበት ወቅት አስታውቀዋል፡፡
በውይይቱም ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሊባኖስ፣ ኩዌት፣ ኦማን፣ ኳታር እና ባህሬን የተውጣጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተገኝተው ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸው ኢትዮጵያውያኑ በፈተና ህይዎት ውስጥ ሆነው ለሃገራቸው እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸው መንግስትም የዜጎች መብት ተጠብቆ እንዲሰሩ ለማድረግ ከየሀገራቱ መንግሥታት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት አድርጓልም ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ንጉሱ ጥላሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የኢሚሬቶች ቆይታ በተመለከተ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ የዶ/ር ዐቢይ ጉብኝት እንደ ሃገር ብዙ ጥቅሞች የተገኙበት ነው ብለዋል፡፡ በተለይም የዜጎችን መብትና ክብር እንዲጠበቅ ከማድረግ አንስቶ የማምለኪያ ቦታዎችን እስከማስለቀቅ የደረሰ ጠቀሜታ ነበርም ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ንጉሱ ገለጻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቆይታቸው የዜጎች ጥቅምና መብት፣የዜጎች ክብር መጠበቅ፣የአምልኮ ቦታዎችን ማስፈቀድና አቅም ያላቸው በልማት እንዲሳተፉ ለማድረግ የሚያስችሉ ጉዳዮች ተነስተዋል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በነበራቸው ቆይታም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውንን ህጋዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን ከሀገሪቱ መንግስት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ደግሞ የጉዞ ሰነድ በማጣት እና በከፋ ችግር ውስጥ ሆነው ከሀገር እንዳይወጡ ለዓመታት ተከልክለው የቆዩ 137 ኢትዮጵያውያንም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አብረው ሃገራው ገብተዋል ብለዋል አቶ ንጉሱ ጥላሁን።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይትም ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ዜጎች ያሉባቸው ችግሮች እንዲፈቱ ከስምምነት መደረሱንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሃገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመክፈት ከስምምነት ተደርሷል። በጉዞው በተደረገ የዲፕሎማሲ ስራ በአቡዳቢ ለኢትጵዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህንጻ ማሰሪያ ቦታም መፈቀዱ የተገለጸ ሲሆን በዱባይ እና ሻርጃ ግዛቶች አማካይ ስፍራ ለፕሮቴስታንት አማኞችም የጸሎት ቦታ በኤክስፖ 2020 ከሚሰራ ህንፃ እንዲሰጥ መወሰኑን ነው የተገለጸው፡፡