የማይፈቱ ከሆነ ሰላማዊ የትግል አማራጮችን እንደሚተገብር አስታውቋል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የታሰሩ አመራርና አባላቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲፈቱ አሳሰበ
አመራርና አባላቱ ’በቂ ባልሆነ መረጃ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ብቻ’ በገዢው መንግስት መታሰራቸውን ያስታወቀው ንቅናቄው በተጠቀሰው ጊዜ በአስቸኳይ የማይፈቱ ከሆነ ሁሉንም የሰላማዊ ትግል አማራጮች እንደሚተገብር አስታውቋል፡፡
ለዚህም አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎቹን ህዝብንም ጭምር በማስተባበር የካቲት 22/2012 ዓ.ም በተመረጡ የአገሪቱ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ እና የካቲት 26 እና 27/2012 ዓ.ም ደግሞ አድማ እንደሚጠራ ገልጿል፡፡
ለሰላማዊ ትግሉ ስኬት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅቶች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ መቀመጡን ያስታወቀም ሲሆን ከመጋቢት 3/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ሕዝባዊ እምቢተኝነትን እንደሚያካሂድም ይፋ አድርጓል፡፡
የንቅናቄው ብሄራዊ ምክር ቤት ከሰሞኑ (ጥር 16 እና 17፣ 2012 ዓ.ም) 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ፤ ከምርጫ ዝግጅት፤ ከታሠሩ የንቅናቄው አመራሮችና አባላት፤ ከታገቱ አማራ ተማሪዎች እና ከሌሎችም ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ውይይቶችን አድርጎ ውሳኔዎችን እና አቅጣጫዎችን ስለማስቀመጡም ተነግሯል።