ናሚቢያ ለቲክቶክ ጤና ጣቢያ ውስጥ የደነሱ ነርሶች ላይ ምርመራ ከፈተች
ነርሶቹ የስነ-ምግባር ደንብ በመጣስና የተቋሙን መልካም ስም በማጥፋት ክስ ተመስርቶባቸዋል
ነርሶቹ አንድ ታካሚን በተሳካ ሁኔታ ካዋለዱ በኋላ ደስታቸውን በዳንስ መግለጻቸውን ተናግረዋል
ናሚቢያ ለቲክቶክ ጤና ጣቢያ ውስጥ የደነሱ ነርሶች ላይ ምርመራ ከፈተች።
ሁለት የናሚቢያ ሰልጣኝ ነርሶች ጤና ጣቢያ ውስጥ ሲጨፍሩ የሚያሳይ ቪዲዮ ቲክቶክ ላይ ከለጠፉ በኋላ ውዝግብ ገጥሟቸዋል።
ሻርሜን ኬንድራ እና ስማርት ሙራንዳ የተባሉት የጤና ባለሞያዎች የነርስ መለያ ልብስ (ዩኒፎርም) ለብሰው ባዶ የታካሚ አልጋ ፊት ለፊት ሲደንሱ ታይተዋል።
ነርሶቹ አንድ ታካሚን በተሳካ ሁኔታ ካዋለዱ በኋላ ደስታቸውን በዳንሱ መግለጻቸውን ተናግረዋል።
የግል የሆነው ዌልዊቺያ ጤና ማሰልጠኛ ማዕከል የቲክቶክ ዳንሱን ተቀባይነት የሌለው ባህሪ ነው በማለት ሰልጣኝ ነርሶቹ በስነ-ምግባር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ፊት እንዲቀርቡ አድርጓል ነው የተባለው።
የናሚቢያን ጋዜጣ ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው ቪዲዮው የተቀረጸው ከሁለት ሳምንት በፊት በጤና ጣቢያው ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ አስተያየቶች የተሰጡበት እና በሰፊው የተሰራጨው ቪዲዮ አሁን በለጠፈችው ነርስ ተሰርዟል።
የዌልዊቺያ ጤና ጣቢያ ሁለቱ ሰልጣኞች የተማሪ የስነ-ምግባር ደንብ በመጣስና የተቋሙን መልካም ስም በማጥፋት ክስ መስርቶባቸዋል።
የሀገሪቱ የተማሪዎች ህብረት ግን የጤና ተቋሙን እርምጃ ሚዛናዊነት የጎደው ሲል ከዚህ ቀደም በነበሩ ተመሳሳይ ጭፈራዎች ላይ እርምጃ አለመውሰዱን ወቅሷል።
ህብረቱ ሁለቱ ተማሪዎች በማስጠንቀቂያ ብቻ ሊታለፉ ይገባል ብሏል።