ከህዋ ላይ የመሬትን ገጽታ የሚያሳየውን ታዋቂ ምስል ያነሱት አሜሪካዊ ህይወታቸው አለፈ
የ“አፖሎ 8” ጠፈርተኛው ዊልያም አንደርስ የሚያበሯት አውሮፕላን ተከስክሳ ነው በ90 አመታቸው የሞቱት
አንደርስ በ1968 ወደ ጨረቃ ሰዎችን ይዛ የተወነጨፈችው መንኮራኩር አብራሪ ነበሩ
ከህዋ ላይ የመሬትን ገጽታ የሚያሳዩ ምስሎችን በማንሳት እውቅናን ያተረፉት አሜሪካዊው ዊሊያም አንደርስ ህይወታቸው አለፈ።
አንደርስ ብቻቸውን ሲያበሯት የነበረች “ቲ-34” አነስተኛ አውሮፕላን በሰሜናዊ ሲያትል መከስከሷ ተሰምቷል።
ልጃቸው ግሬግ “ጎበዝ አብራሪ” የነበሩት አንደርስ በ90 አመታቸው ህይወታቸው ማለፉን ማረጋገጡን ሬውተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካው የጠፈር ድርጅት (ናሳ) ሃላፊ ቢል ኔልሰን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፥ የቀድሞው የአየር ሃይል አብራሪ “ጠፈርተኛ ለሰው ልጆች ሊሰጥ የሚችለውን ትልቁን ስጦታ አበርክቶልናል” ብለዋል።
የቀድሞው ጠፈርተኛ እና የአሁኑ የአሪዞና ግዛት ሴናተር ማርክ ኬሊም “(አንደርስ) እኔን ጨምሮ በጠፈርና አሰሳ መሰማራት የምንፈልግ ሰዎችን አነቃቅቶናል” ሲሉ ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካውን የጠፈር ድርጅት (ናሳ) በ1963 የተቀላቀሉት ዊሊያንም አንደርስ በ1968 ወደ ጨረቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎችን ይዛ የተወነጨፈችው መንኮራኩር አብራሪ ነበሩ።
የ”አፖሎ 8” ተልዕኮ እነ አንደርስ ጨረቃ ላይ ሳያርፉ 10 ጊዜ ዞረዋት ወደ መሬት እንዲመለሱ ማስቻሉ ይታወሳል።
ይህ ታሪካዊ ጉዞ ዊሊያም አንደርስ የመሬትን ውብ ገጽታዎች በካሜራዎቹ እንዲያስቀር አድርጎት አሁንም ድረስ ምስሎቹ ለመሬት ጥናትና ተያያዥ ጉዳዮች ጥቅም ላይ ይውላሉ።
ምስሎቹ አለማቀፍ የአየር ንብረት ጥበቃ ንቅናቄዎች እንዲፈጠሩና የምድር ቀን መከበር እንዲጀምርም ምክንያት ሆነዋል።
በ1969 ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲረግጥ ባስቻለችው “አፖሎ 11” ተጠባባቂ አብራሪ የነበሩት ዊሊያም አንደርስ በ1970ዎቹም በኖርዌይ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።
አሁንም ድረስ የሚታወሱት ግን በአፖሎ 8 የጨረቃ ተልዕኮ ባነሷቸው ድንቅ ምስሎች ነው።