ኤልኒኖ 110 ሚሊየን ሰዎችን የምግብ ድጋፍ ጠባቂ ያደርጋል - ናሳ
የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ማዕከል (ናሳ) ኤልኒኖ እስከ 2024 አጋማሽ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ተጽዕኖውን ያሳርፋል ብሏል
የኤልኒኖ ክስተት ድርቅና ጎርፍን በማስከተል ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር በመፍጠር ላይ ይገኛል
የኤልኒኖ ክስተት እስከ 2024 አጋማሽ በአፍሪካ፣ እስያ እና አሜሪካ የምግብ ዋስትና ችግር እንደሚፈጥር የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ማዕከል (ናሳ) አስታወቀ።
የአለም የዝናብ ወቅት እየረበሸ የሚገኘው የኤልኒኖ ክስተት ከ110 ሚሊየን በላይ ሰዎችን የምግብ ድጋፍ ጠባቂ እንደሚያደርግም ነው የናሳ ተመራማሪዎች አዲስ ሪፖርት ያመላከተው።
የውቅያኖሶችን የሙቀት መጠን የሚጨምረው የኤልኒኖ ክስተት የማዕከላዊ እና ምስራቃዊ ፓስፊክ ውቅያኖስን ሙቀት ከመደበኛው በላይ እንዲሆን ያደርጋል።
ይህም በአፍሪካ ቀንድ እና ደቡባዊ አሜሪካ ድርቅን ያስከትላል ነው ያለው ናሳ።
በደቡባዊ አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ደቡባዊ እስያ ድርቅን እንደሚያስከትል ሪፖርቱ ጠቁሟል።
በ2023 መጨረሻ ብርቱ ተጽዕኖውን አድርሶ በ2024 አጋማሽ ያበቃል የተባለው የኤልኒኖ ክስተት በበርካታ የአለማችን ክፍሎች የምግብ ዋስትና ችግርን እንደሚያስከትልም ተገልጿል።
ከሁለት እስከ ሰባት ዓመታት ልዩነት የሚከሰተው ኤልኒኖ ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ ከባድ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ነው።
ክስተቱ ምድር እስካሁን ካስተናገደችው ጠንካራ የተባለ ሲሆን፥ ካለፉት 130 ዓመታት ወዲህም ከባድ የሙቀት መጠን የተመዘገበበትም ነው።
በ2015 የኢንዶኔዥያ ጫካዎችን በእሳት አጋይቶ በተዘዋዋሪ በተፈጠረ የአየር ብክለትም ከ100 ሺዎች በላይ ሕይወት የቀጠፈ ክስተት መሆኑ ይታወሳል።
በኤልኒኖ ምክንያት ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ከ35 ዓመታት ወዲህ ተመዝግቦ የማያውቅ የድርቅ መጠን መመዝገቡም አይዘነጋም።
ከ40 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያንን ለከፋ የምግብ እጥረት ያጋለጠው ኤልኒኖ አሁንም ድረስ ጠባሳው አልሻረም የሚለው ናሳ፥ እስከ 2024 አጋማሽ የሚያደርሰው ጉዳትም ከ110 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ይነካል ብሏል።