አሜሪካ ከ50 ዓመታት በኋላ ተመራማሪዎችንና መሳሪያዎቻቸውን ወደ ጨረቃ ለመላክ እየሰራች ነው
የአሜሪካው ናሳ “አርቴሚስ 1” የተባለ ሮኬትን ወደ ጨረቃ ለማስወንጨፍ ያደረገው ሙከራ ለሁለተኛ ጊዜ መክሸፉ ተሰምቷል።
የናሳ ተመራማሪዎች በትናትናው እለት ሮኬቱን ለማስወንጨፍ የሚረዳውን የጠፈር ማስወንጨፊያ ስርዓት ለማስጀምር በተደጋጋሚ ቢሞክሩም ለሁለተኛ ጊዜ ሳይሳካቸው ቀርቷል።
የሮኬቱ ማስወንጨፍ ለሁለተኛ ጊዜ ሳይሳካ የቀረው በማስወንጨፊያው ላይ ባጋጠመው የነዳጅ መፍሰስ እንደሆነም ታውቋል።
ይህንን ተከትሎም የዘርፉ ባለሙያ ኢንጂነሮች በሮኬቱ ላይ ድጋሚ ፍተሻ ያደርጋሉ የተባለ ሲሆን፤ ይህም ጊዜ ሉወስድ ይችላል ተብሏል።
ፍተሸው ከማስወንጨፊያ ስፍራ ይልቅ በመስሪያ ቦታው ላይ ተወስዶ ሊካሄድ እንደሚችል እና ይህም የሮኬቱን የማስወንጨፊያ ጊዜ እስከ ጥቅምት ወር ሊያዘገየው ይችላል ነው የተባለው።
ናሳ ሮኬቱን ባሳለፍነው ሰኞ ወደ ጨረቃ ለማስወንጨፍ ሞክሮ የነበረ ሲሆን፤ ሆኖም ግን አራቱ ትላልቅ ሞተሮች በትክክለኛ የሥራ ሙቀት ላይ መሆናቸውን ተቆጣጣሪዎች ማረጋገጥ ባለማቻላቸው ተቋርጦ ነበር።
ሮኬቱን የማስወንጨፍ ሙከራ ከትናትናው ጋር ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ መሳካት ግን አልቻለም።
አሜሪካ ከ50 ዓመታት በኋላ ተመራማሪዎችንና መሳሪያዎቻቸውን ወደ ጨረቃ ለመላክ እየሰራች ሲሆን፤ ይህም የአፖሎ ፕሮጀክት እአአ በ1972 ካበቃ በኋላ የተሰራ ነው።
100 ሜትር የሚረዝመው ሮኬት አላማው ኦሪዮን የተባለውን ካፕሱል ወደ ጨረቃ ለማድረስ አላማ ኖሮት የተሰራ መሆኑንም ከናሳ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።