ብሄራዊ ባንክ ከብር ቅያሬው በኋላ በሁሉም ባንኮች 580 ሺህ ዜጎች የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል አለ
ብሄራዊ ባንክ ከብር ቅያሬው በኋላ በሁሉም ባንኮች 580 ሺህ ዜጎች የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል አለ
ኢትዮጵያ በይፋ ብር ከቀየረች ጊዜ ጀምሮ 14 ቢሊዮን ብር ወደ ባንክ ገቢ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ደርጅት(ኢፕድ)ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር ይናገር አዲሱ ብር በመላ አገሪቱ ባሉ የባንክ ቅርንጫፎች 99 ነጥብ 9 በመቶ መዳረሱን በቃለ ምልልሱ አንስተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሁሉም ባንኮች 580 ሺህ ዜጎች የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ዶ/ር ይናገር ገልጸዋል፡፡
በ580 ሺህ አዲስ የሂሳብ አካውንቶች ውስጥም በ14 ቀናት ውስጥ ብቻ 14 ቢሊዮን ብር ወደ ባንክ ገቢ መደረጉን ያነሱት ገዥው በነባር አካውንት ውስጥ የገባው የገንዘብ መጠንን በተመለከተ ደግሞ ተጠቃሎ ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡
መንግስት ሙስናን ለመካከልና ከኢኮኖሚ ውጭ ያለውን ብር ወደ ባንክ ለማስገባት በማሰብ አዲስ የብር ኖት ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የብር ለውጥ መደረጉን ይፋ ባደረጉበት ወቅት 2.9 ቢሊዮን የብር ኖቶች መታተማቸውንና ለህትመቱም 3.7 ቢሊዮን ብር ወጭ መደረጉን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡በብር ቅያሬው ከዚህ በፊት ያልነበረ ባለ 200 ብር ኖት የተዋወቀ ሲሆን ነባሮቹ ባለ10፣ባለ50 እና ባለ100 ብር በአዲስ ገጽታ ተቀይረው አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡
አሮጌውን ብር በአዲስ ቀይሮ ለመጨረስ የሶስት ወር የጊዜ ገደብ ተቀምጧል፡፡