የአንድ አመት የስራ ጊዜ የተጨመረለት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምን ምን ስራዎችን ለማጠናቀቅ አስቧል?
በ2014 የተመሰረተው ኮሚሽን ቀሪ ዋና ዋና ተግበራትን ለማከናወን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1 ዓመት ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶታል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/18/243-181628-images-8-_700x400.jpeg)
የኮሚሽነሩ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የኮሚሽኑ የስራ ጊዜ እንዲራዘም ፍላጎት እንደሌላቸው ከዚህ ቀደም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ መናገራቸው ይታወሳል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ባካሄደው 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሦስት ዓመት የስራ አፈፃፀምን ከገመገመ በኋላ ለተጨማሪ 1 ዓመት እንዲራዘም ወስኗል።
ኮሚሽኑ ያላከናወናቸውን ቀሪ ዋና ዋና ተግባራት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቅ ያዘዝው ምክር ቤቱ የ3 አመት የስራ አፈጻጸሙን ገምግሟል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የኮሚሽኑ የስራ ዘመን ለአንድ ዓመት እንዲራዘም የቀረበውን ሀሳብ በ3 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ኮሚሽኑ በየካቲት ወር አጋማሽ 2014 ዓ.ም ከተቋቋመ ጀምሮ ላለፉት ሶስት አመታት ምን አይነት ስራዎችን እንዳከናወነ እና በተጨመረለት የአንድ ዓመት ጊዜ ምን ምን ስራዎችን ለማጠናቀቅ እንዳቀደ ጠይቋል፡፡
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ባለፉት ሶስት ዓመታት ኮሚሽኑ ከፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ከተከሰቱ የሰላም መደፍረሶች ጋር እየተጋለ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳደሮች የአጀንዳ እና የተሳታፊ ልየታ ስራዎችን ማጠናቀቁን አቶ ጥበቡ አንስተዋል፡፡
“በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ትግራይ ክልል ሲቀር ከወረዳ ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ተቋማት የሚወከሉበት የተሳታፊዎች ልየታን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ አጠናቀናል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ በሀገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ከ55 በላይ ፓርቲዎች ተሳትፏቸውን ለማጠናከር እና እምነትን የመፍጠር ተግባራትን አከናውነናል” ብለዋል፡፡
አጀንዳ ማሰባሰብን በተመለከተ ኮሚሽኑ ከአማራ እና ትግራይ ክልል በስተቀር ስራው መጠናቀቁን ያነሱት ቃል አቀባዩ በተጨመረው አንድ አመት ለማጠናቅቅ ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል ዋነኛው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አክለውም “በሀገሪቱ የተለያዩ የሀሳብ ልዩነቶች እና ውዝግቦች ያሉ ቢሆንም እነዚህን ችግሮች በውይይት መቅረፍ የሚያስችል ተቋም ስላልነበረን ኮሚሽኑ በዚህ ረገድ ወይይቶችን ባህል ማድረግ እና ተቃራኒ ሀሳቦች በንግግር መፍታት የሚያስችሉ ባህሎችን ማንበር ላይ ፈተናዎችን አስተናግደናል” ነው ያሉት፡፡
ይህ ሁኔታም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተለያዩ ማህበረሰባዊ ተቋማት በኮሚሽኑ ላይ የእምነት ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች እና የሰላም መደፍረሶች ኮሚሽኑ ባቀደው ጊዜ ስራውን እንዳያጠናቅቅ እና ባሰበው ፍጥነት እንዳይጓዝ መሰናክል ሆነው መቆየታቸው ተነስቷል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ነፍጥ አንግበው ከመንግስት ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኙ አካላትን ማሳተፍን በተመለከተ የኮሚሽኑ ሀላፊነት ብቻ እንዳልሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ታጣቂዎችን ለማሳተፍ እና ለደህንነታቸው ዋስትና ለመስጠት እንደሚችል ኮሚሽኑ ተደጋጋሚ ጥሪ ማቃረቡን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ከዚህ ቀደም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከታጣቂዎች ጋር በፈለጉበት የውጭ ሀገር ለመገናኘት እና ሀሳባቸውን ለመቀበል ጥሪ ቀርቦ እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በሶስት አመቱ ያልተጠናቀቁ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልክቶ ማብራርያ የሰጡት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ በዲያስፖራው የማህበረሰብ ክፍል እንዲሁም በትግራይ እና አማራ ክልል ያሉ ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጣቸው አመላክተዋል፡፡
“በፌደራል ደረጃ ፣ በዲያስፖራው የማህበረሰብ ክፍል እና በሁለቱ ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራዎች ይቀራሉ፤ ቀጥሎም የአጀንዳ ቀረጻ እንዲሁም በሀገራዊ ምክክሩ ውይይት የሚደረግባቸው ሀገራዊ አጀንዳዎችን ዘርዝሮ ይፋ ማድረግ ላይ በተጨመረው አንድ አመት ውስጥ ትኩረት አድርገን እንሰራለን” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ለምክክር ጉባኤው አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ፣ ከህብረተሰቡ ከተሰበሰቡ አጀንዳዎች ለጥናት እና ምርም እንዲሆኑ አድርጎ ማዘጋጀት ፣ በተቀረጹ አጀንዳዎች ላይ መግባባት እንዲፈጠር ማድረግ ላይ ኮሚሽኑ ይሰራል ተብሏል፡፡
የተለያዩ የፖለቲካ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ ጫፍ እና ጫፍ ያሉ አጅንዳዎችን ማቀራረብ ዋነኛ አላማው አድርጎ የተቋቋመው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተጨመረለት አንድ ዓመት ስራውን ለማጠናቀቅ እንደሚጥር ተናግሯል፡፡
የኮሚሽነሩ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ በጥቅምት ወር 2016 ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቀሪ ተግባራትን አስመልክተው ባደረጉት ቃለ ምልልስ “አማራ ክልልን በተመለከተ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን እና መንግስት እና ታጣቂዎች ወደ ድርደር የሚመጡበትን እና የክልሉን ነዋሪዎች ሀሳብ ለማካተት እንዲያግዝ ኢ መደበኛ በሆነ መንገድ እያሳሰብን እንገኛለን” ብለዋል፡፡
የትግራይ ክልል አስመልክተውም “በአመራር ደረጃ ኮሚሽኑ ስራ እንዲጀምር የፍቃደኝነት ችግር የለም፤ ነገር ግን ክልሉ በተፈናቃዮች ጉዳይ፣ አሁን ከሚገኝበት የፖለቲካ ሁኔታ እና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ጥያቄ አለው፤ እሱን በቅርበት ለመፍታት እና በቶሎ ስራ እንድንጀምር ከክልሉ አመራሮች ጋር እየተነጋገርን ነው” ሲሉ አብራርተው ነበር፡፡
ከአራት ወራት በፊት ገደማ ባደረግነው ቃለ ምልለስ አል ዐይን አማረኛ የኮሚሽኑ ጊዜ የሚራዘም ከሆነ እርሶ በሃላፊነት ይቀጥላሉ ወይ? ሲል ፕሮፌሰር መስፍንን ጠይቋል፡፡
“አሁን ባለው ሁኔታ የኮሚሽኑ ጊዜ እንዲራዘም አልፈልግም እንዲራዘምም አልጠየቅንም፤ በእርግጥ የትግራይ እና አማራ ክልሎች ላይ ያሉ ሁኔታዎች ባይዙን ኑሮ ከዚህ ቀደም ብለንም የምንጨርስበት ሁኔታ ነበር፤ ነገር ግን ከሎጂስቲክ ከትራንስፖርት እና ከሰላም ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ስራችንን በተገቢው ፍጥነት እንዳናከናውን እንቅፋት ሆነውብናል፤ አሁን እየሰራን ያለነው በቀረን ጊዜ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ነው እድሜውን የማራዘም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀላፊነት ነው እኔ በግሌ ብጠይቀኝ ግን የኮሚሽኑ እድሜ እንዲራዘም ፍላጎት የለኝም” ማለታቸው ይታወሳል፡፡