የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር ይሰጣል ተባለ
የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና በያዝነው ዓመት የካቲት ወር ላይ መሰጠቱ ይታወሳል
ፈተናው የተራዘመው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ነው ተብሏል
የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር ይሰጣል ተባለ።ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ እንዳሳወቀው የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ጥቅምት 2014 ዓ.ም ላይ ለመስጠት ፕሮግራም ተይዟል።
በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በትግራይ ክልል ካሉ ተማሪዎች ውጪ 620 ሺህ ተማሪዎች ተመዝግበው ፈተናውን በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ የኤጀንሲው መረጃ ያስረዳል።የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በሰጡት መግለጫ ኤጀንሲው በማንኛውም ሰዓት ፈተናውን መስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቋል።
በሀገሪቱ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የኢኮኖሚክስ ትምህርት ባለመሰጠቱ ፈተናው እንደማይሰጥ ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደዚህ ዓመት ተሸጋግሮ ከየካቲት 29 ጀምሮ እስከ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በመላው አገሪቱ የተሰጠ ሲሆን ወደ ዩንቨርሲቲ መግባት የቻሉ ተማሪዎች ወደየተመደቡባቸው ዩንቨርሲቲዎች በመግባት ላይ መሆናቸውን የኤጀንሲው መረጃ ይጠቁማል።
ሀገር አቀፍ ፈተናውን ከወሰዱ ከ250 ሺህ በላይ ተፈታኝ ተማሪዎች ውስጥ 55 ነጥብ 7 በመቶዎቹ ከ350 በላይ አምጥተው ነበር።
የዓመቱ ከፍተኛ ውጤትም 669 ሆኖ በተመዘገበበት የ2012 ዓ.ም ፈተና ውጤቱ ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን 702 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት እንዳመጡ መገለጹ አይዘነጋም።