ለ12ኛ ክፍል ፈተና ቀን ተቆርጦ ለህዝቡ ሊነገር እንደሚገባ ፓርላማው አሳሰበ
የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ በኦንላይን ይሰጣል መባሉ የሚታወስ ነው
ሚኒስቴሩ የፈተና ስርቆትን የሚያስቀር ቴክኖሎጂ ለመጠቀም በመታሰቡ ምክንያት የፈተና ጊዜው ሊዘገይ መቻሉን አስታውቋል
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚሰጥበት ቀን ተቆርጦ ለተማሪዎች እና ለወላጆች ሊነገር እንደሚገባ አሳሰበ፡፡
ማሳሰቢያውን የሰጠው የትምህርት ሚኒስቴርን የ2013 ዓ/ም የግማሽ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት የገመገመው የምክር ቤቱ የግብርና፣ አርብቶ-አደር እና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በ2012 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና መውሰድ የነበረባቸው ተማሪዎች እስካሁን ፈተናውን አልወሰዱም ያሉት የቋሚኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ አልማዝ መሰለ ፈተናውን ባለመውሰዳቸው ወላጆቻቸው ጭምር ለከፍተኛ ስነ ልቦናዊ ጫና መዳረጋቸውን በአንጽኦት ተናግረዋል፡፡
ጫናው በተያዘው ዓመትም እንዳይቀጥል ያላቸውን ስጋት የገለጹም ሲሆን ፈተናው የሚሰጥበት ቀን ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ተማሪዎች በፈተናው መዘግየት እና የፈተና ጊዜው በውል ባለመታወቁ ምክንያት ለዓይነተ ብዙ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡
በማህበራዊ ገጾችም ስለዚሁ ጉዳይ የተጻፉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
ለዚህ ምላሽ የሰጡት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ የፈተና ስርቆትን የሚያስቀር ቴክኖሎጂ ለመጠቀም በመታሰቡ ምክንያት የፈተና ጊዜው ሊዘገይ ችሏል ብለዋል፡፡
ከ4 መቶ ሺህ የሚልቁ ታብሌት ኮምፒውተሮች ተገዝተው ወደ ሀገር መግባታቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ተፈታኝ ተማሪዎችን በማለማመድ ፈተናውን ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነን ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ማስረዳታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ሚኒስቴሩ ከአሁን ቀደም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ በኦንላይን ይሰጣል ሲል ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡