ኢዴፓ በአማራ ክልል የተጠራውን ሰልፍ የክልሉ መንግስት መከልከሉን አውግዟል
አብን መግለጫ እንዳይሰጥ መከልከሉን ገለጸ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዛሬ ሊሰጠው የነበረውን መግለጫ የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳስተጓጎለበት አስታወቀ፡፡
ፓርቲው በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ እንዳለው “ፓርቲያችን በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውንና እየተፈፀመ ያለውን ተከታታይ የዘር ፍጅት ለማውገዝ ጥቅምት 18 ቀን በአማራ ክልል እንዲሁም ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፎችን ቢጠሩም መምራት እንዳንችል ተደርገናል” ብሏል፡፡
የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ ቴዎድሮስ ኃይለማሪያም (ዶ/ር) ፣ ፓርቲው መግለጫውን እንዳይሰጥ መከልከሉን ገልጸው ቢሮውም በፖሊስ መከበቡን አንስተዋል፡፡
የአብን ከፍተኛ አመራሮች ስለሰላማዊ ሰልፉ ዝርዝር ሁኔታዎች በዋና ጽ/ቤቱ እየመከሩ ባሉበት ሰዓት የአዲስ አበባ ፖሊስ ከበባ በመፈፀም መግባትና መውጣት እንደማይቻል መግለጹን ነው ንቅናው ያስታወቀው፡፡
አብን የታቀደውን ሰልፍ በተቋማዊ ማዕከላዊነት ለመምራት እና ለሰልፉ የተዘጋጁ ሎጂስቲኮችን ለማንቀሳቀስም ሆነ ሰልፉን ለመምራት ስራ አስፈፃሚው ወደ ክፍለ ሀገር እንቅስቃሴ ለማድረግ መቸገሩን ገልጿል፡፡ በዚህ የተነሳም ንቅናቄው የጠራውን ሰልፍ በኃላፊነት መምራት የማይችል መሆኑን ገልጿል፡፡
በቀጣይ መደረግ ስለሚገባቸው የትግል አካሄዶች በተመለከተ እናሳውቃለን” ብሏል ፓርቲው፡፡
በተያያዘ የኢ.ዴ.ፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ አንድ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገ መንግስታዊ መብት አለው ያለ ሲሆን መንግስት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ( አብን) ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል በተለያዪ ከተሞች የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በክልሉ መንግስት መከልከሉን አውግዟል፡፡
የክልሉ መንግስት በፓርቲው ላይ የጣለውን የመብት ክልከላ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ሲልም ኢዴፓ ጠይቋል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ትናንት በሰጡት መግለጫ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ለነገ (ረቡዕ) የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ የአማራ ክልል እንዲረጋጋ ለማይፈልጉ ሀይሎች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚያመች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የተፈጥሮ አደጋ (የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ) በተከሰተበት እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዓለም አቀፍ አጀንዳ በሆነበት በዚህ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ህጋዊ አይደለም በማለት ክልሉ ለሰልፉ እውቅና አለመስጠቱን ተናግረዋል፡፡