ኢትዮጵያን ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመታደግ የብሔራዊ ደህንነት እርምጃ እንዲወሰድ አብን ጥሪ አቀረበ
በትግራይ ክልል የተማሪዎችንና የሊቪል ዜጎችን ደህንነት መንግስት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል
ከምርጫው ጋር በተያያዘ የምርጫ ቦርድ የሚያሳልፈውን ውሳኔ እናከብራለን ብሏል
ማዕከላዊ መንግሥትና በየደረጃው ያሉ መንግስታዊ አካላት ሀገሪቱ ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመታደግ በግልጽ ከመወሰን አንስቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ ደህንነት እርምጃ እንዲወስዱ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ጥሪ አቀረበ።
ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አቶ ጣሂር መሐመድ መንግሥት ልዩ የደህንነት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ብለዋል።
አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የ“ትህነግ” ቡድን መልሶ በተቆጣጠረው በትግራይ ክልል የተማሪዎችንና የሲቪል ዜጎችን በአጠቃላይ የትግራይን ህዝብ ደህንነት መንግስት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ፓርቲው ጠይቋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ሁኔታ አብን እንደደሚያሳስበው ገልጿል።
የትግራይ ህዝብ በመካከሉ ለሚገኙ ተማሪ ልጆቹ አስፈላጊውን ጥበቃና ክብካቤ እንዲያደርግም አብን ጥሪ አቅርቧል።
አብን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ሀገራችን ስለገጠማት የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያን ለመታደግ በአንድነት እንዲሰለፉም ጠይቋል።
በወታደራዊ ኃይል የሚገኘው ድል ዳግም በዲፕሎማሲው አውድማ እንዳይነጠቅ መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ትግል እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።
ከምርጫው ጋር በተያያዘም የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንብር አቶ የሱፍ ኢብራሂም “የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እናከብራለን፤ ተቋሙ እንዲጠናከርም እንሰራለን” ብለዋል።
መንግስት መመስረት ያለበት በምርጫ ብቻ መሆን አለበት አለበት ብሎ እንደሚያምንም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በመግለጫው አስታውቋል።