“ከሌሎች በላይ ኢትዮጵያዊ ነን አንልም ከእኛ በላይ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ግን እርግጠኛ ነን”-የአብን ሊቀመንበር
“ከሌሎች በላይ ኢትዮጵያዊ ነን አንልም ከእኛ በላይ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ግን እርግጠኛ ነን”-የአብን ሊቀመንበር
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) መጪውን ሃገራዊ ምርጫ ታሳቢ ያደረጉ የፖሊሲ አማራጮችን በማዘጋጀት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦቹ ዝግጅት በመገባደድ ላይ ነው ያሉት አዲሱ የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ (ረዳት ፕሮፌሰር) ምናልባትም በቅርቡ ሚዲያዎችን ጠርተው ሊያስተቹ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ንቅናቄው ቀደም ሲል ባደረገው ጥናት መሰረት የህገ ደንብ እና የፕሮግራም ማሻሻያዎችን ስለማድረጉም ትናንት ማክሰኞ የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ማሻሻያው ፓርቲው ያለበትን የቤት ስራ በተቀላጠፈ መንገድ ለማከናወንና ተቋማዊ አደረጃጀቱን ለማጠናከር ያስችለዋል ተብሏል በመግለጫው፡፡
ለመሆኑ አብን ምን ዓይነት ማሻሻያዎችን ነው ያደረገው?
ወርሃ ሰኔ መባቻ 2010 ዓ/ም ላይ በባህርዳር መስራች ጉባዔውን አድርጎ በይፋ መመስረቱን ያስታወቀው አብን ብሄራዊ ምክር ቤት በማቋቋም ነበር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን የነበረው፡፡
ሆኖም ይህ “ሲመሰረት የነበረው የአደረጃጀት መዋቅር በሚፈለገው ፍጥነት ሊያስኬድ የማይችል እንደሆነና ብዙ መስተካከል መታረም ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ” መገንዘቡን ነው ያስታወቀው፡፡
5 አባላት ያሉትን ቡድን በማቋቋም ሲያደርግ በነበረው ጥናት የተገኙ ውጤቶችም፣ሊሰራ የሚፈልጋቸውን ነገሮች በተፋጠነ መልኩ መስራት እንዳይችል ያደረጉትን እነዚህን የአደረጃጀት መዋቅሮች ማሻሻል እንደሚያስፈልገው ነው ያመለከቱት፡፡
በዚህም መሰረት የዞን አመራሮች ውክልና ያልነበረበትንና በዋናነትም የክትትል ብቻ ተግባራትን ያከናውን የነበረውን ብሄራዊ ምክር ቤቱን እንደገና በማዕከላዊ ኮሚቴነት አደራጅቷል፡፡
“የተፋጠነ ስራ እንዳንሰራ እንዳደረገን ገምግመናል” ያለውን የስራ አስፈጻሚ አባላት ቁጥርም ከ13 ወደ 9 ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡
ህገ ደንቡንም ምርጫ ቦርድ ያወጣቸውን አዳዲስ ህግጋት ታሳቢ አድርጎ እንዳሻሻለና የፓርቲ ፕሮግራሙንም “መሰረታዊም ባይሆን አንዳንድ ማሻሻያዎችን” አድርጎ ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
ይህ ጠንካራ እና በምርጫ ለአሸናፊነት የተዘጋጀ አብንን ለመፍጠር እንደሚያስችል ነው ሊቀመንበሩ የተናገሩት፡፡
ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ማሻሻያዎችን እያደረገ የሚቀጥለው ያሉት አብን በምርጫው አሸናፊ ሆኖ ለመምጣት የሚያስችለውን ሰፊ ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
“ከሌሎች በላይ ኢትዮጵያዊ ነን አንልም ከእኛ በላይ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ግን እርግጠኛ ነን”
ሊቀመንበሩ “አብን ጽንፈኛ ነው፤ ከኢትዮጵያዊነት ጋር እንዴት ሊቆም ይችላል” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“ጽንፈኛ ማለት ትርጉሙ አይገባንም፤ በእርግጥ ሃሜቱን እንሰማለን ከየት እንደመጣ እና ምንን ታሳቢ እንዳደረገ፣ይሄን በማስፋፋት ሊገኝ የታሰበውን ፖለቲካዊ ትርፍ እናውቃለን አትራፊው ማን እንደሆነም የምናጣው አይደለም” ያሉት አቶ በለጠ፣ አማራ “ማንም ጤነኛ የሆነ ሰው ሊመሰክረው የሚችል” በሚል የገለጹትንና ”የደረሰበትን ስርዓታዊ ጭቆና” ለመታገል በሚል አብን መመስረቱን ገልጸዋል፡፡
“ፖለቲካዊ ውክልና ሳይኖረው በሌሎች ችሮታ የሚኖር በሚሊዬን የሚቆጠር አማራ እንዳለ እኛም እናውቃለን ሌላውም ያውቀዋል” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች መፍትሄ ያገኙ ዘንድ በአማራነት መደራጀታችን ምናልባት ጽንፈኛ እንድንባል እንዳስቻለን እናውቃለንም ብለዋል፡፡
“ይህ ራሱን ከኢትዮጵያዊነት አንጻር ከሚመለከተው አማራ ጭምር የሚስተዋል ነው፤ ግን ቀርበው አልተረዱንም ወይም አልተገነዘቡንም” ያሉም ሲሆን ”እኛ ከኢትዮጵያ ያነሰ ከኢትዮጵያ የጠበበ ራዕይ የለንም ይሄም ሊሰመርበት ይገባል” ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ የአማራ ሃገሩ ነች፤ በዚህች ሃገር እኩልነት ፍትህና ሰላሙ ተረጋግጦ ከሌሎች ህዝቦች ጋር እኩል ቆሞ ኃላፊነቱንም እኩል ተጋርቶ እንዲኖር ነው የምንፈልገው” ካሉ በኋላ፣ “እኛ ከሌሎች በላይ ኢትዮጵያዊ ነን አንልም ከእና በላይ ኢትዮጵያዊ እንደ ሌለ ደግሞ እርግጠኛ ሆነን እንናገራለን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡