አዲስ የሽግግር መንግስት መመስረትን እንደማይደግፍ አብን አስታወቀ
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ቆይቶ የሽግግር ሂደቱን መምራቱ ካሉት አማራጮች በአንፃራዊነት እንደሚሻልም ንቅናቄው ገልጿል
ብሔራዊ የውይይት ኮሚሽን እንዲቋቋምም ጠይቋል
አዲስ የሽግግር መንግስት መመስረትን እንደማይደግፍ አብን አስታወቀ
ከሰሞኑ አስቸኳይ ስብሰባውን ያደረገው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሃገሪቱ ለገባችበት ፖለቲካዊ ቀውስ አዲስ የሽግግር መንግሥት መፍትሄ እንደማይሆን አስታውቋል፡፡
ከዚህ ይልቅ የተወሰነ የሽግግር ጊዜ መፍጠር የተሻለ አማራጭ ነው ያለው ንቅናቄው ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መቆየትና የሽግግር ሂደቱን መምራት ካሉት አማራጮች በአንፃራዊነት የተሻለ ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል፡፡
መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች በልሂቃኑ መካከል ከሚደረግ ውይይትና ድርድር ከሚመነጭ ፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈታሉ ብሎ እንደሚያምንም ነው ያስታወቀው፡፡
የማያቋርጥ የድርድርና እርቅ ሂደት እንደሚያስፈልግ በመጠቆምም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማኅበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላት ያካተተና ለሕዝብ ተወካዮች ተጠሪ የሆነ የብሔራዊ ውይይት ኮሚሽን እንዲቋቋም ጠይቋል፡፡
መንግሥት ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ ብሔራዊ ውይይት እንዲጀመር ለማድረግ ዋስትና እንዲሰጥ፣ የ1999 ዓ.ም ብሔራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ተሰርዞ ለተከሰቱት ጉዳቶች ፍትኃዊ ማካካሻ እንዲደረግና ቀጣዩም ቆጠራ ሳይንሳዊና ገለልተኛ በሆነ ተቋም እንዲካሄድ፣ የሕገ መንግሥት ለውጥ ወይም ማሻሻያ እንዲደረግ እና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በመንግስት በኩል የተለየ ዝግጁነት እንዲኖርም ንቅናቄው ጠይቋል፡፡
አገር ለማተራመስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን አጥብቄ እታገላለሁም ብሏል፡
ቀደም ሲል ያስቀመጣቸውን አቋሞች በተመለከተ ከመንግሥትና ከተለያዩ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር እየተነጋገረ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑንም ነው አባላትና ደጋፊዎቹ ከጎኑ እንዲቆሙ ባስታወቀበት ጥሪው የገለጸው፡፡