የአሜሪካ እና ብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ዩክሬን የሚላኩ የጦር መሳሪያዎችን ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ከሩሲያ ጋር ውጊያ ውስጥ ለምትገኘው ዩክሬን የከባድ መሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱን ገለጸ፡፡
የኔቶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለሁለት ቀናት በብራሰልስ ስብሰባ አድርገው የነበረ ሲሆን በስብሰባው ላይ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ኩሌባ ተገኝተዋል ተብሏል፡፡
የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫ ሀገራቱ ለዩክሬን የሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከርና በፊት ከነበረው እንዲጨምር ስምምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት የኔቶ አባል ሀገራት ተጨማሪ ከባባድና ጠንካራ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ዩክሬን ለመላክ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡ አሁን ወደ ዩክሬን ይላካሉ የተባሉት የጦር መሳሪያዎች፤ በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል ያለውን ጦርነት እንዲባባስ ሊያደርገው እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምዕራባውያን ወደ ዩክሬን የጦር መሳሪያ ከመላክ እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡
የብሪታኒያዋ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስ አሁን ለዩክሬን የሚደረገው ድጋፍ ወታሮቿ በሶቪየት ዘመን ከተሰሩ የጦር መሳሪየዎችን እንዲላቀቁ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ ይሁንና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የትኛውን የጦር መሳሪያ ለዩክሬን እንደሚላክ ከመናገር ተቆጥበዋል ተብሏል፡፡
የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ ደግሞ አባል ሀገራቱ ከስብሰባ በኋላ ብዙ ስራ እንዲሰሩ ይጠበቃል የሚል ማሳሰቢየ ከሰጡ በኋላ ለዩክሬን የሚያስፈልግ ቁሳቁስ ለማቅረብና ብዙ ለመስራት ዝግጁ ናቸው ብለዋል፡፡
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ኩሌባ የኔቶ አባል ሀገራት አውሮፕላኖችን፣ መሬትን መሰረት ያደረጉ ሚሳኤሎችን፣የአየር መከላከያና ሌሎች የጦር መሳሪዎችን ለሀገራቸው እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ “እያወራሁ ያለሁት ለሳምንታት ሳይሆን ለቀናት ነው፤ ድጋፋችሁ ዘግይቶም ሊመጣ ይችላል” ሲሉ ድጋፉ በፍጥነት እንዲደረግና እንዳይዘገይ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚነስትር አንቶኒ ብሊንከን የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን ልዩነት መፍጠር ሚችል የጦር መሳሪያ እንዴት መላክ እንዳለባቸው እየተነጋገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡አንቶኒ ብሊንከንም ወደ ዩክሬን ይላካሉ የተባሉትን የጦር መሳሪዎች ዝርዝር ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡