“የኔቶ አባል እንዳንሆን የከለከሉን ሜርክልና ሳርኮዚ ወደ ቡቻ እንዲመጡ እጋብዛለሁ”- የዩክሬን ፕሬዝዳንት
የቀድሞ መሪዎች ዩክሬን የኔቶ አባል እንዳትሆን አድርገዋል በሚል እየተወቀሱ ነው
አንጌላ ሜርክል የ2008 ውሳኔያቸውን እንደተከላከሉ ገልጸዋል ተብሏል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ “የኔቶ አባል እንዳንሆን የከለከሉን አንጌላ ሜርክል እና ኒኮላስ ሳርኮዚ ዛሬ ግፍ ወደተፈጸመበት ቡቻ እንዲመጡ እጋብዛለሁ” ሲሉ የቀድሞ የጀርመንና የፈረንሳይ መሪዎችን ኮነኑ።
ዘለንስኪ ይህንን ያሉት የቀድሞዋ የጀርመን መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ከ 14 ዓመት በፊት ዩክሬን የኔቶ አባል እንዳትሆን ውሳኔ ወስነው ነበር ከሚል በማንሳት መሆኑን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚም በተመሳሳይ በአውሮፓውያኑ 2008 ላይ በሮማኒያ ዋና ከተማ ቡካሬስት በተደረገ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጉባዔ ላይ ዩክሬን የድርጅቱ አባል እንዳትሆን አድርገዋል በሚል ከሜርክል እኩል እየተወቀሱ ነው።
የሩሲያ መንግስት ዜና አገልግሎትም ዩክሬን የኔቶ አባል እንዳትሆን ያደረጉት የቀድሞዎቹ የጀርመንና የፈረንሳይ መሪዎች ናቸው ሲል ዘግቧል።
ከ14 ዓመት በፊት በተደረገው የሮማኒያው ጉባዔ አልባኒያ እና ክሮሺያ የኔቶ አባል ለመሆን ሂደቶችን ማጠናቀቃቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በአውሮፓውያኑ 2009 ድርጅቱን ተቀላቅለዋል።
በወቅቱ ዩክሬን እና ጆርጂያ ወደፊት አባል ይሆናሉ ቢባልም ሁለቱም አሁን የድርጅቱ አባሎች አይደሉም። የቀድሞዋ የጀርመን መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በወቅቱ ያራመዱትን አቋምና የወሰኑትን ውሳኔ ዛሬ መከላከላቸው ተሰምቷል።
በ2008 በተደረገው የኔቶ ጉባዔ ዩክሬንና ጆርጂያ ለኔቶ ዋጋ ያለው አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተገልጾ በቀጣይም አባል እንደሚሆኑ የተገባው ቃል ሳይሳካ ዩክሬን መወረሯ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪን አበሳጭቷል።
ዛሬ በዩክሬን ቡቻ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ በኋላ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ፤ የቀድሞውን የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ እና የጀርመን የቀድሞ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክልን ግፍ ወደተፈጸመበት ቡቻ እንዲመጡ ``እጋብዛቸዋለሁ`` ብለዋል።
ዩክሬንና ጆርጂያ በቀጣይ አባል እንደሚሆኑ በ 2008 በኔቶ ስብሰባ ቢነገራቸውም ከዛ በኋላ ሀገራት በ2009 እና በ2020 የኔቶ አባል ሀገራት ሆነዋል። በቅርቡ ማለትም በ 2020 ሰሜን ሜቄዶኒያ የኔቶ አባል ስትሆን የዩክሬን ጉዳይ አልተነሳም ነበር።
ዘለንስኪ ዩክሬን የኔቶ አባል ያልሆነችው ሩሲያን በመፍራትና በመለማመጥ እንደሆነ አሳውቀዋል። ቀደም ሲል ዘለንስኪ ኔቶ “ደካማና እርምጃ የማይወስድ ተቋም ነው” ማለታቸው ይታወሳል።